ሀገሩ አልጄሪያ ነው፤ ሰጢፍ ግዛት በሀገሪቱ ካሉ ዋና ዋና ሕዝብ በብዛት ከሚኖርባቸው ግዛቶች አንዷ ነች፡፡ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በኩል ደግሞ ዐይነል ከቢራ ከተማ ትገኛለች፡፡ በአንዱ ቀዝቃዛ ማለዳ፤ በአንድ የአካባቢው የቁርኣን መምሕር አነሳሽነት የፈጅር ሰላት የአዛን ጥሪ ከመሰማቱ በፊት እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናትን በመቀስቀስ ለሰላት በጀመዐ መሄድ ተጀመረ፡፡ በመጀመርያው ቀን ስድስት ሕጻናት ተሳታፊ ሆኑ፡፡ የሕጻናቱ ቡድን ከእንቅልፋቸው ነቅተው ወደ መስጅድ በማቅናት በፈጀር ሰላት ከፊት ረድፍ መሰለፋቸው እንግዳ ነገር ነበር፡፡
የእነዚህ ሕጻናት በቡድን ሆነው ወደ መስጂድ ሲጓዙ የሚያሳዩ ቪድዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲሠራጭ ግን አንዱ ለሌላው ብርታት ሆኖ በሌሎች የአልጄሪያ ግዛቶችም በተመሳሳይ ተነሳሽነቶች ተጀመሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት የተሳታፊዎች ቁጥር በሺሕዎች ይቆጠራል፡፡ በቡርጅ ቡ አሬሪጅ ብቻ ከ80 በላይ ሕጻናት በመደበኛነት ይታደማሉ፡፡ በዚያ የተለየው ነገር አንድ የአካባቢው አስተባባሪ ዓብዱረሕማን ለተባለ ሕጻን በፈጅር ሰላት በመታደሙ የዑምራ ሽልማት ማበርከቱ ነው፡፡ ሽልማቱ በዓብዱረሕማን ብቻ አልቆመም፤ ሦስት ተጨማሪ የዑምራ ሽልማቶች ለሌሎች ሕጻናት ተሰጥቷል፡፡
ይህ ከአልጄሪያ የተነሳ ትዕይንት በማኅበራዊ ሚዲያ ተሠራጭቶ መላውን የሙስሊሙን ዓለም ልብ ነክቷል፡፡ ተነሳሽነቱ “ሪጃሉል ፈጅር” የሚል ሥያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ በቀጥተና ትርጉሙ “የማለዳ ሰዎች” ወይም “የንጋት ጀግኖች” እንደማለትም ነው፡፡ ከአልጄሪያ ሲሻገር ሞሮካውያን ዘመቻውን የተቀላቀሉት “ፉርሳን አል ፈጅር” በሚል ሥያሜ ነው፡፡ “የንጋት ፈረሰኞች” የሚል ትርጉም በያዘው እንቅስቃሴ ሕጻናት ለንጋት ሰላት ተሰባስበው የሚያሳዩ ፎቶግራፍ እና ቪድዮ እያጋሩበት ለሌሎች ብርታት እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ግብጽ የአልጄሪያውን “ሪጃሉል ፈጅር” ስትጠቀም፤ በዮርዳኖስ ደግሞ “ነሻሚል ፈጅር” በመባል ይጠራል፡፡ ከሞሮኮ፣ ዮርዳኖስና ግብጽ ባሻገር በእኛዋ ጎረቤት ሱዳንም በርካታ ሕጻናት ለፈጅር ሰላት ሲገኙ የሚያሳዩ ቪድዮዎች እየተጋሩ ይገኛል፡፡ የዮርዳኖሱ ዘመቻ መስራች አይመን አል በለዊ እንደተናገሩት፤ በፈጅር ሰላት ወቅት የመስጂዱ ታችኛው ክፍል በሰጋጆች በመሙላቱ፣ አብዛኛውን ጊዜ ለጁመዐ አልያም ለረመዳን ካልሆነ በስተቀር የማይከፈተው ሁለተኛ ፎቅ እንዲከፈት ተገደዋል፡፡
የዚህ እንቅስቃሴ ፋይዳ ሰላት ከመስገድም በላይ ነው፡፡ ለሕጻናት ሰዓት አክባሪነትን፣ ሥነ ሥርዐትን፣ ንጽሕናንና ለሃይማኖታዊ ግዴታዎች ክብር መስጠትን ያስተምራል፡፡ ስለ መልካም ሥነ ምግባር በቃል ከማስተማር ይልቅ፣ በተግባራዊ ልምምድ በጎ ልማዶችን ያስተዋውቃቸዋል፡፡
“ዓለም አቀፉ የሙስሊም ሊቃውንት ኅብረት” ተነሳሽነቱን በሕጻናት ልብ ውስጥ የፈጅር ሰላት ፍቅርን የሚተክልና አዲሱን ትውልድ ከልጅነቱ ጀምሮ ከመስጂድ ጋር የሚያስተሳስር “የተባረከ ጥረት” ነው ሲል አወድሶታል፡፡ ኅብረቱ እንደገለጸው፤ ይህ ተነሳሽነት “በሁሉም የሙስሊም ሀገራት ሊስፋፋ የሚገባው” ነው፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያዎች በርካቶች ይህን እንቅስቃሴ “ትውልድን የማነጽ” መንገድ ብለውታል፡፡ አንዳንዶች ሕጻናቱ አጥንት የሚሰብር ቅዝቃዜን ተቋቁመው በፊት ረድፍ ላይ መሰለፋቸው አዋቂዎችን ጭምር እያነቃቃ መሆኑን ጽፈዋል፡፡
በርግጥ ተነሳሽነቱ ተቺዎችንም አላጣም፡፡ አንዳንድ ተችዎች ይህ እንቅስቃሴ “የሕጻናትን የእንቅልፍ ሰዓት ይሻማል” እንዲሁም “በትምህርታቸው ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ለዚህ ምላሽ የሚሰጡ ሐኪሞች፤ ሕጻናት ቀደም ብለው ከተኙና ወደ ዘጠኝ ሰዓት ያህል እንቅልፍ ካገኙ፣ በማለዳ መንቃት ትኩረትንና አካላዊ ንቃትን እንደሚሻሽል የሚያሳዩ ጥናቶችን አቅርበዋል፡፡
ክርክሩ የከረረው የአልጄሪያው ዕለታዊ ጋዜጣ “አል ፈጅር” ሥራ አስኪያጅ ሀዳ ሐዛም በቲክቶክ የቀጥታ ሥርጭት ተነሳሽነቱን ከተቹ በኋላ ነው፡፡ ሰውዬው በሕጻናት እንቅልፍና ትምህርት ላይ ይደርሳል ካሉት ጉዳት ባሻገር የሕጻናቱ ደኅንነት ጋር በተገናኘ ውንጀላ አቅርበዋል፡፡ ይሁን እንጂ “ኦሪየንት” የተባለ ሬድዮ የጋዜጣው ሥራ አስኪያጅ ካሉት ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተመዘገበ ክስተት አልተገኘም ሲል ዘግቧል፡፡ ይህ ንግግር የፓርላማ አባላትን አስቆጥቶ ዑመር ማእመር የተባሉ የፓርላማ አባል ለፍትህ ሚኒስቴር ደብዳቤ እንዲጽፉ አድርጓል፡፡ የአልጄሪያ የሃይማኖት ጉዳዮችና አውቃፍ ሚኒስቴርም መስጂዶችና ኢማሞችን ሰድበዋል በሚል ክስ መስርቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለመዳኘት ለፊታችን እሑድ ቀጠሮ ይዟል፡፡
ንጋት ላይ ፀሓይን ቀድመው መስጂድ የሚደርሱት ልጆች መንፈሣዊ ጀብድ፤ በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ዘንድ ትኩረትን እየሳበ አንዳንዶችም ዘመቻውን ተቀላቀሉን እያሉ ይገኛሉ፡፡ ስለ ጉዳዩ ዘለግ ያለ ጽሑፍ ያቀረበው ዳዕዋ24 ድረ ገጽ በጽሑፉ ማጠቃለያ ላይ ይህን አስፍሯል፡-
የስክሪን ሱስና እስከ እኩለ ሌሊት ማምሸት በበዛበት በዚህ ዘመን፣ በማለዳ ነቅቶ ወደ መስጂድ መሄድን የሚለምድ ሕጻን ሰላትን ብቻ ሳይሆን ሥነ ሥርዐትን፣ ኃላፊነትንና የማኅበረሰቡ አካል የመሆንን ስሜትም ይማራል፡፡ ይሁን እንጂ ተነሳሽነቱ እንዲሳካ የወላጆችን ፈቃድ፣ ሕጻናት በሰዓቱ እንዲተኙ የሚያስችል ዝግጅት እንዲሁም በመስጂድ ውስጥ ለደኅንነታቸውና ለጤናቸው የሚደረግ ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ነገሮች ከተሟሉ፣ “ሪጃሉል ፈጅር” ለእያንዳንዱ የሙስሊም ማኅበረሰብ ምሣሌ መሆን የሚችል ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












