የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከቻይናው ቲደብሊው ሆልዲንግ ሊሚትድ ጋር በኢትዮጵያ የንግድ የመማሪያ መጻሕፍት ማተሚያ እና አሳታሚ ተቋም ለመገንባትና ለማስተዳደር የሚያስችል የጋራ ኩባንያ ለማቋቋም ስምምነት ተፈራርሟል። የጋራ ኩባንያው የመነሻ ኢንቨስትመንት 30 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚደርስ ተገምቷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ኅዳር 16/2019 ባሰራጨው መረጃ፤ ስምምነቱ ቲደብሊው ሆልዲንግ 51 በመቶ የኩባንያው ድርሻ ሲኖረው፣ ቀሪውን 49 በመቶ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ይይዛል። የቻይናው ኩባንያ የማምረቻ ቴክኖሎጂ፣ ማሽነሪዎች፣ ቴክኒካዊ ልምድና የአሠራር አቅም የማቅረብ እንዲሁም የፋብሪካውን ግንባታና ሥራ በመምራት ኃላፊነት ይወስዳል።
የታቀደው ፋብሪካ የትምህርት ቤት መማሪያ መጻሕፍትንና የመምህራን መመሪያዎችን ጨምሮ የትምህርት ቁሳቁሶችን የማተም፣ የመጠረዝና የማሸግና የማሰራጨት ሥራዎችን ያከናውናል።
ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እንደገለጸው፣ ኢንቨስትመንቱ በኢትዮጵያ እያደገ ባለው የመማሪያ መጻሕፍት ፍላጎትና በአገር ውስጥ የማተም አቅም መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ነው።
በተጨማሪም ከውጭ በሚገቡ የትምህርት ቁሳቁሶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ፣ ተመጣጣኝነታቸውንና ጥራታቸውን ለማሻሻልም ያለመ ነው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆንልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ብሩክ ታዬ፣ ሽርክናው በመማሪያ መጻሕፍት ዘርፍ ለረዥም ጊዜ የዘለቁ ክፍተቶችን ለመሙላት፣ የአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማጠናከርና የበለጠ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንደሚረዳ ገልጸዋል። (ሚንበር ቲቪ)












