Homeዜናና ወቅታዊዜናየእስልምናን ክብር የሚዳፈር አስተያየት የሰጠውን ግለሰብ “ጊዜ ሳይሰጠው ለሕግ አቅርቦ ለሕዝብ እንዲያሳውቅ”...

የእስልምናን ክብር የሚዳፈር አስተያየት የሰጠውን ግለሰብ “ጊዜ ሳይሰጠው ለሕግ አቅርቦ ለሕዝብ እንዲያሳውቅ” የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ለመንግሥት ጥሪ አቀረቡ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ፤ በማኅበራዊ ትስስር መድረክ የእስልምናን ክብር የሚዳፈር አስተያየት የሰጠውን ግለሰብ፤ “ጊዜ ሳይሰጠው ለሕግ አቅርቦ ለሕዝብ እንዲያሳውቅ” ለመንግሥት ጥሪ አቀረቡ፡፡ ፕሬዝዳንቱ ጥሪውን ባቀረቡት ንግግር፤ ጠቅላይ ምክር ቤቱ፤ “ሕግና ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ ክስ መሥርቶ [በጉዳዩ ላይ] እየሔደበት ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ይህን የተናገሩት ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 3/2017 በሰጡት መግለጫ ነው፡፡ በዚህ መግለጫ ላይ ባለፉት ቀናት በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ የእስልምናን እንዲሁም የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)ን ክብር የሚዳፈር አስተያየት የሰጠው ግለሰብ ጉዳይ እንዲሁም የ1446 ዓ.ሂ የሐጅ ምዝገባ ጉዳይ ዋንኛ ትኩረት ተደርጎ ተነስቷል፡፡

ቀዳሚውን ጉዳይ በተመለከተ የተናገሩት ሸይኽ ሐጅ ኢብራሂም፤ “ሀገርን ለማበላሸት እና አንድነት ለመናድ የሚተጋ” ነው ያሉት ግለሰብ፤ ተደብቆ ቢቆይም በቁጥጥር ስር መዋሉ አይቀርም ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሎ ለሕግ እስከሚቀርብ ድረስ “ከእኛ የሚጠበቀው በትዕግሥት ዱዓ እያደረግን መጠበቅ ነው” ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በዚህ ንግግር ወቅት የሚመሩት ጠቅላይ ምክር ቤት፤ በግለሰቡ ላይ “ሕግ እና ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ ክስ ተመሠርቶ እየሔደበት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ የክሱን ሒደት ዝርዝር ጉዳይ እንዲሁም የደረሰበትን ደረጃ አላብራሩም፡፡

ጠቅላይ ምክር ቤቱ የካቲት 30/2017 ባወጣው መረጃ፤ በግለሰቡ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሙስሊም ሕግ ባለሞያዎች ማኅበር “ክስ መመሥረት የሚያስችለውን የወንጀል ምርመራ ሒደት ማጠናቀቁን” በይፋዊ ማኅበራዊ ትስስር ገጹ ገልጾ የነበረ ቢሆንም፤ በዛሬው መግለጫ ላይ ሳይጠቀስ አልፏል፡፡ “ሚንበር ቲቪ” በጉዳዩ ላይ በቅርቡ ምሥረታውን ካደረገው ማኅበር ስለ ሒደቱ ለማጣራት ያደረገው ጥረት ምላሽ ባለማግኘቱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

በዛሬው መግለጫ ላይ የተነሳው ሌላኛው ጉዳይ ባለፈው ወር ምክር ቤቱ ሲያከናውነው የቆየው የ1446 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ምዝገባ ጉዳይ ነው፡፡ ማብራሪያውን የሰጡት ፕሬዝዳንቱ፤ ለሐጅ ምዝገባ የተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ መጠናቀቁን ተከትሎ ከኅብረተሰቡ “ብዙ ጥያቄ እየቀረበልን ነበር” ብለዋል፡፡ ቀድሞ ለተላለፈው ውሳኔ መነሻ ሆኖ የነበረው የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር አስተላልፎት የነበረው መመርያ መሆኑን የጠቀሱት ሸይኽ ሐጅ ኢብራሂም፤ በተደረገው ንግግር የቀን ጭማሪ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የዘንድሮ ሐጅ ምዝገባ ጊዜ እስከ ረመዳን 29 ድረስ መራዘሙን ይፋ አድርገዋል፡፡  

ጠቅላይ ምክር ቤቱ በዘንድሮ ዓመት ለሐጅ ሥነ ሥርዐት ይመዘገባሉ በሚል ያስቀመጠው ኮታ 10 ሺሕ እንደሆነ ቀድሞ አሳውቆ እንደነበር ይታወቃል። ምዝገባው የተጀመረው ጥር 15/2017 ሲሆን፣ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው የካቲት 22/2017 (ሻዕባን 30/1446 ዓ.ሂ) ነው። ምዝገባው መራዘሙን በተመለከተ የምክር ቤቱ ሌሎች ኃላፊዎች ከጋዜጠኞች የቀረበላቸውን ጨምሮ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚሁ ወቅት እስካሁን የተመዘገበው ምዕመን ቁጥር ስንት እንደረሰ ጥያቄ ቢቀርብም፤ “ከተጠበቀው በታች” የሚል ምላሽ በመስጠት ትክክለኛውን ቁጥር ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡ “ሚንበር ቲቪ” ለማጣራት ባደረገው ሙከራ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ እስካሁን ድረስ ለሐጅ የተመዘገቡ ኢትዮጵዊያን ምዕመናን ቁጥር እስከ ማከሰኞ መጋቢት 2/2017 ድረስ 4 ሺሕ 12 ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular