በ1446 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ለመከወን በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በኩል የተመዘገቡ ምዕመናን ቁጥር አራት ሺሕ መሆኑን “ሚንበር ቲቪ” ሰምቷል፡፡ ጠቅላይ ምክር ቤቱ፤ ቀድሞ ያስቀመጠውን የጊዜ ሠሌዳ ማራዘሙን ይፋ እንደሚያደረግ ይጠበቃል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ በዘንድሮ ዓመት ለሐጅ ሥነ ሥርዐት ይመዘገባሉ በሚል ያስቀመጠው ኮታ 10 ሺሕ እንደሆነ ቀድሞ አሳውቆ ነበር። ምዝገባው የተጀመረው ጥር 15/2017 ሲሆን፣ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው የካቲት 22/2017 (ሸዋል 30/1446 ዓ.ሂ) ነው። ይሁን እንጂ በተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ ይመዘገባል ተብሎ የሚጠበቀው የምዕመናን ቁጥር ሳይሞላ መቅረቱ የጊዜ ሠሌዳውን እንዲያራዝም ተገዷል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በክንውኑ ላይ የሚሳተፉት ምዕመናንን ሲመዘግቡ የነበሩ ጣቢያዎች ምዝገባውን እንደሚቀጥሉም ሚንበር ቲቪ ያገኘው መረጃ ያመለክታል። እንደ መረጃው ከሆነ፤ ምዝገባው የሚቀጥለው እስከ መጋቢት 17/2017 (ረመዳን 26/1446) ድረስ ነው። ጠቅላይ ምክር ቤቱ ጉዳዩን በማስመልከት በነገው እለት ይሰጣል ተብሎ ከሚጠበቀው መግለጫ አስቀድሞ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ የጊዜው ሠሌዳ መራዘሙን መጋቢት 1/2017 በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ አድርጓል።
ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ የተሳተፉ ምዕመናን ቁጥር 12 ሺሕ ነበር።
የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒቴር ባወጣው ይፋዊ መረጃ ባለፈው ዓመት ከመላው ዓለም በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ የተሳተፉ ምዕመናን ቁጥር ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












