Homeዜናና ወቅታዊዜናሐሳብን በነጻነት መግለጽ መብትን “የሌላውን እምነት ለመስደብ ወይም ለማዋረድ የሚያውሉ” ላይ ሕጋዊ...

ሐሳብን በነጻነት መግለጽ መብትን “የሌላውን እምነት ለመስደብ ወይም ለማዋረድ የሚያውሉ” ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ የሃይማኖት ጉባዔ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ጉባዔ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን “የሌላውን እምነት ለመስደብ ወይም ለማዋረድ የሚያውሉ” ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ የጠየቀው በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ ነው፡፡ በቅርቡ “አንዳንድ የኦርቶዶክስ ክርስትና አማኝ ነን የሚሉ ግለሰቦች” በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዓ.ወ) ላይ የሠነዘሩትን “ድፍረት የተሞላበት ክብረ ነክ እና ፀያፍ ንግግር” አውግዟል፡፡

ጉባዔው ይህን የገለጸው ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 2/2017 በጽሕፈት ቤት በሰጠው መግለጫ ወቅት ነው፡፡ የጉባዔውን አቋም በንባብ ያሰሙት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ የእምነት ነጻነት እና የማምለክ መብት ለሁሉም ማኅበረሰቦች የተጠበቀ መሆኑን በመጥቀስ፤ ይህ መብት “የሌሎች አማኖችን መብት በሚጋፋና ስሜት በመንካት” ለጠብ ማነሳሻነት ሲውል “በዝምታ ሊታለፍ” እንደማይገባውም ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ “አንዳንድ የኦርቶዶክስ አማኝ ነን” በሚሉ ሲል የገለጻቸው ግለሰቦች፤ በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ላይ “ድፍረት የተሞላበት ክበረ ነክና ጸያፍ ንግግር” ማድረጋቸውን ማስታወስ፤ ይህ የሙስሊሙን ወገን ብቻ ሳይሆን ሰላም ወዳዱን ወገን አሳዝኗል ብሏል፡፡ “ኢ-ሥነ ምግባራዊ እና ሕገ ወጥ” ያለው ይህ ተግባር የትኛውንም የሃይማኖት ተቋም የማይወክል፣ ይልቁንም የሚወገዝ ተግባር መሆኑንም ገልጿል፡፡

የዛሬው መግለጫ የመጣው ባለፉት ቀናት በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ፤ አንድ ግለሰብ የእስልምናን እንዲሁም የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ክብር የሚነካ ንግግር ማሠራጨቱን ተከትሎ በመድረኩ ተሳታፊዎች ተቃውሞ ከተሰማ በኋላ ነው፡፡

ጉዳዩን በማስመልከት ሰኞ መጋቢት 1/2017 መግለጫ ያወጣው የኢትየጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ ድርጊቱን በማውገዝ የጥላቻ ንግግር ያደረጉ ግለሰቦች “አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የፍትሕ፣ የፀጥታ እና የደኅንነት አካላት “የሕግ ተጠያቂነት ለማምጣት እንዲሠሩ” አሳስቦ ነበር፡፡ በዚሁ መግለጫ፤ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጉዳዩ ከዚህ በላይ ከመካረሩ በፊት የጋራ አቋም በመያዝ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ተጠይቋል፡፡

ጠቅላይ ምክር ቤቱ የካቲት 30/2011 ባወጣው መረጃ፤ በግለሰቡ ጉዳይ ወደ ክስ ለመመሥረት የሚያስችለውን የወንጀል ምርመራ ሒደት ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡ “ሚንበር ቲቪ” ሒደቱን በተመለከተ ባደረገው ማጣራት፤ ምክር ቤቱ ግለሰቡን የተመለከቱ ሠነዶችን እያሰባሰበ እንደሚገኝ ማረጋገጥ ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ቀጣዩን ርምጃ በተመለከተ እስካሁን ድረስ ምክር የሰጠው ማብራሪያ የለም፡፡

ይህን ተከትሎ ጉባዔው በሰጠው መግለጫ፤ ከሰሞኑ የተፈጸመው ድርጊት በሁሉም ሃይማኖቶች ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን የሚወገዝ መሆኑንም በማስታወስ፤ ድርጊቱ በወንጀል የሚያስጠይቅ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጉባኤው መተዳደሪያ ደንቡ ላይ ማሻሻያዎች ማድረጉን ገልጿል፡፡ እንደ መግለጫው ከሆነ፤ የተሻሻለው ደንብ በተቋማት መካከል “አለመከባበርን የሚሰብኩ፣ ጥላቻን የሚቀሰቅሱና ግጭትን የሚያብብሱ ተንኳሽና ክብረ ነክ ንግግሮችንና ተግባራትን የሚፈጸጽሙ ግለሰቦችና ቡድኖችን” በራሳቸው ተቋም ተጠያቂ የሚያደርግ ሥርዐት እንዲኖር የሚያደርግ ድንጋጌ ያካተተ ነው፡፡

“የችግሩ ስፋትና ጥልቀት እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞም” ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከአባል የሃይማኖት ተቋማት የሚወከሉ “የሕግና አግባብነት ያላቸው ባለሙያዎች የሚካተቱበት የተከላካይ ግብር ኃይል አደረጃጀት” በጊዜያዊነትና በቋሚነት በማደራጀት የቅደመ መከላከል ሥራዎች ለመሥራት እንደተዘጋጀም ተገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular