የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ የኢስላምንና የነቢዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ክብር የሚነካ የጥላቻ ንግግር ያደረጉ ግለሰቦች ላይ የፀጥታና የሕግ አካላት ተጨማሪ ጥፋት ከመከተሉ በፊት አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱ አሳሰበ። ማሳሰቢያውን የሰጠው ዛሬ ሰኞ መጋቢት 1/2017 ባወጣው መግለጫ ነው፡፡
ምክር ቤቱ በመግለጫው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ውዝግብና ግጭት ለመፍጠር የሚሠሩ አካላት እየተበራከቱ መምጣታቸውን ገልጿል፡፡ በተለይም የእስልምናን መልካም እሴቶች እና የነቢዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ከብር በመዳፈር ሕዝበ ሙስሊሙን የሚያስቆጡ የጥላቻ ንግግሮች በሥፋት እየተሠራጩ መሆናቸውን መረዳቱን ጠቁሟል፡፡
እነዚህ አካላት ከዛሬ ነገ ሕጋዊ ርምጃ ተወስዶባቸው ከጥፋታቸው ይታረማሉ በሚል ቀና እሳቤ ጉዳዩን በትዕግስት ሲከታተል ቆይቷል ያለው የምክር ቤቱ መግለጫ፤ በተደጋጋሚ ተከስቶ በቸልታ እየታለፈ ነው ያለውን የኢስላምንና የነቢዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ክብር የሚነካ የጥላቻ ንግግር ያደረጉ ግለሰቦች አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የፍትሕ፣ የፀጥታና የደኅንነት አካላት የሕግ ተጠያቂነትን ለማምጣትና መሰል ጥፋቶች እንዳይደገሙ ከመቼውም ጊዜ በላይ በልዩ ትኩረት እንዲሠሩ አሳስቧል፡፡
አያይዞም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ይህ በአደባባይ የተላለፈ የጥላቻ ንግግርና ሀይማኖታዊ ትንኮሳ በሕዝበ ሙስሊሙ ላይ የፈጠረውን ህመም በአግባቡ በመረዳት የሚመለከታቸው የፀጥታና የሕግ አካላት ተጨማሪ ጥፋት ከመከተሉ በፊት አስቸኳይ ርምጃ እንዲወስድም ጠይቋል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ መግለጫውን እንዲያወጣ መነሻ የሆነውን ምክንያት አልገለጸም፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ቀናት በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ አንድ ግለሰብ በተደጋጋሚ የእስልምናን እና የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)ን ክብር የሚነካ ተደጋጋሚ ንግግር ማቅረቡ ከፍተኛ ቁጣ መቀስቀሱን ሚንበር ቲቪ ተመልክቷል። (ሚንበር ቲቪ)












