ቻይና በዐረብ አገራት የሚመራውን የጋዛ መልሶ ማልማት በመገደፍ፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነዋሪዎችን ለማፈናቀል ያቀረቡትን ዕቅድ ውድቅ ማድረጓን ያሳወቀችው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ነው፡፡ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ይህንኑ መናገራቸውን ዥንዋ ዘግቧል፡፡
ሚኒስትሩ በቻይና ዓመታዊ የሕግ አውጭ ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት ሲናገሩ፤ “ሀገራችን በግብፅ እና በሌሎች የዐረብ አገራት የተጀመረውን ጋዛ ውስጥ ሰላም ለማስፈን የተያዘውን ዕቅድ ትደግፋለች። ጋዛ የፍልስጤም ሕዝብ ንብረት ስትሆን፣ የፍልስጤም ግዛትም የማይነጠል አካል ነች” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የጋዛን ሁኔታ በግዳጅ መቀየር “አዲስ ሁከት” ይፈጥራል ያሉት ዋንግ፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲያስፈጽም፣ የሰብዓዊ ርዳታ እንዲጨምር እንዲሁም “ፍልስጤማውያን መሬታቸውን እንዲያስተዳድሩ” የሚለውን መርሕ እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቻይና የመካከለኛውን ምሥራቅ ቀውስ ለመፍታት የፍልስጤም ሀገረ መንግሥት መመሥረት አለበት የሚለውን የሀገራቸው አቋም በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
በቻይና ድጋፍ ያገኘው በዐረብ ሀገሮች ተቀባይነት ያገኘው የጋዛ መልሶ ማልማት ምክረ ሐሳብ የቀረበው በግብጽ አማካኝነት በካይሮ በተደረገው የዐረብ ሊግ ጉባዔ ላይ ነው፡፡ በተያዘው ሣምንት ማክሰኞ በተደረገው ጉባዔ በቀረበው ምክረ ሐሳብ፤ ለጋዛ መልሶ ግንባታ የተጠየቀው ገንዘብ 53 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ምክረ ሐሳቡ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን ፍልስጤማዊያንን ከጋዛ የማፈናቀል ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ በማድረግ፤ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ሥፍራ ሳይዘዋወሩ ግንባታው እንዲከናወን የሚጠይቅ ነው፡፡
የመልሶ ግንባታው መሪ እንዲሆን የታጨው መቀመጫውን ራምአላህ ያደርጋል የተባለ የፍልስጤም መንግሥት ሲሆን፣ በማሕሙድ አባስ ለሚመራው የፍልስጤም አስተዳደር ድጋፍ ይሰጣል የተባለ የጋዛ አስተዳዳር ኮሚቴ እንደሚዋቀርም ተገልጿል፡፡
ገለልተኛው ኮሚቴ የሚዋቀረው ከምሑራን እና ከፖለቲካ ድርጅት አባልነት ነጻ በሆኑ ግለሰቦች እንደሚሆኑም የተዘጋጀው ሠነድ ላይ ሠፍሯል፡፡ በዚህም የፍልስጤም አስተዳደር ጋዛን በሒደት ሙሉ ለሙሉ መልሶ ማስተዳደር እንዲጀምር ይደረጋል፡፡ በዚህ ሒደት ጋዛን እ.አ.አ ከ2007 አንስቶ እያስተዳደረ የሚገኘው ሐማስ እንዲገለል የሚደረግ ይሆናል፡፡ ምክረ ሐሳቡን የፍልስጤሙ ሐማስ ሲቀበል፤ አሜሪካ እና እስራኤል ውድቅ አድርገውታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












