Homeዜናና ወቅታዊዜናበግብጽ የቀረበው የጋዛ መልሶ ግንባታ ዕቅድ፤ በቀጣይ ሳምንት በኢስላማዊ ትብብር ሀገራት ትብብር...

በግብጽ የቀረበው የጋዛ መልሶ ግንባታ ዕቅድ፤ በቀጣይ ሳምንት በኢስላማዊ ትብብር ሀገራት ትብብር ድርጅት ሊጸድቅ ነው

ግብጽ፤ ለጋዛ መልሶ ግንባታ ያቀረበችው ምክረ ሐሳብ በካይሮ በተደረገው የዐረብ ሊግ ጉባዔ ቀርቦ ተቀባይነት ማግኘቱ ታውቋል፡፡ ማክሰኞ በተደረገው ጉባዔ በቀረበው ምክረ ሐሳብ፤ ለጋዛ መልሶ ግንባታ የተጠየቀው ገንዘብ 53 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ምክረ ሐሳቡ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን ፍልስጤማዊያንን ከጋዛ የማፈናቀል ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ በማድረግ፤ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ሥፍራ ሳይዘዋወሩ ግንባታው እንዲከናወን የሚጠይቅ ነው፡፡

የመልሶ ግንባታው መሪ እንዲሆን የታጨው መቀመጫውን ራምአላህ ያደርጋል የተባለ የፍልስጤም መንግሥት ሲሆን፣ በማሕሙድ አባስ ለሚመራው የፍልስጤም አስተዳደር ድጋፍ ይሰጣል የተባለ የጋዛ አስተዳዳር ኮሚቴ እንደሚዋቀርም ተመላክቷል፡፡ ገለልተኛው ኮሚቴ የሚዋቀረው ከምሑራን እና ከፖለቲካ ድርጅት አባልነት ነጻ በሆኑ ግለሰቦች እንደሚሆኑም የተዘጋጀው ሠነድ ላይ መስፈሩን ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡ በዚህም የፍልስጤም አስተዳደር ጋዛን በሒደት ሙሉ ለሙሉ መልሶ ማስተዳደር እንዲጀምር ይደረጋል፡፡ በዚህ ሒደት ጋዛን እ.አ.አ ከ2007 አንስቶ እያስተዳደረ የሚገኘው ሐማስ እንዲገለል የሚደረግ ይሆናል፡፡

እንደ ሠነዱ ከሆነ፤ በጋዛ ለሚመሠረተው አስተዳደር የፖሊስ ኃይል የማሠልጠን ኃላፊነት የሚወስዱት ግብጽ እና ጆርዳን ይሆናሉ፡፡ ሌሎች ፖለቲካዊ እና የፋይናንስ ድጋፎችን በተመለከተ ከሁለቱ ሀገሮች በተጨማሪ ተጨማሪ ሀገራት ሊሳተፉ እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡

በዚህ አግባብ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በዌስት ባንክ እና ጋበዛ የሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲያሠፍር ጥቆማ ቀርቧል፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ የተነሳው ሌላኛው ጉዳይ እንደ ሐማስ ዐይነት የታጠቁ ቡድኖች በአስተዳደሩ የሚኖራቸው ሚና ነው፡፡ ለምክረ ሐሳቡ ትግበራ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የተጠቀሱት ቡድኖች ጉዳይ ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ሊያገኝ የሚችለው የፍልስጤማዊያን መብት ሲከበር መሆኑም ተገልጿል፡፡ ለዚህም ፍልስጤማዊያን የራሳቸውን ሀገር እንዲመሠርቱ ከማድረግ ውጪ አማራጭ የተለየ አማራጭ እንደሌለ ምክረ ሐሳቡ ይጠቁማል፡፡

በቀረበው ምክረ ሐሳብ መሠረት የጋዛ መልሶ ግንባታ የተለያዩ ደረጃዎች ይኖሩታል፡፡ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል በተባለው በመጀመሪያው ስድስት ወር፤ የጋዛ ፍርስራሾችን የማጽዳት ሥራ ይከናወናል፡፡ በቀጣይ በሁለት ዙር በአጠቃላይ አራት ዓመት ከመንፈቅ ይፈጃል ተብሎ በእቅድ የተያዘው የከተማዋ መልሶ ግንባታ መሠረተ ልማቶችን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች የተካተቱበት ነው፡፡ በጋዛ መልሶ ግንባታ 1.5 ሚሊዮን ሰዎችን በተገጣጣሚ ቤቶች ለማስጠለል ሰባት አካባቢዎች ተመርጠዋል፡፡

በግብጽ የቀረበው የጋዛ መልሶ ግንባታ ምክረ ሐሳብ በሁለት ጎራ በተቃርኖ የተሞሉ አስተያየቶችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡ የፍልስጤሙ ሐማስ ምክረ ሐሳቡን ሲቀበል፤ አሜሪካ እና እስራኤል ውድቅ አድርገውታል፡፡ የምክረ ሐሳቡ አዘጋጅ ግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለእስራኤል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስትሩ በድር ሙሐመድ አሕመድ አልዓጢ፤ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን “ግትር እና ጽንፈኛ” በማለት ወርፈዋቸዋል፡፡ ጨምረውም “ያለ ሉዓላዊት የፍልስጤም ሀገር ምሥረታ በእስራኤልም ሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ማስፈን የማይታሰብ” መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በስብሰባው ላይ የተሳተፉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው ጋዛን መልሶ ማቋቋም ከፍተኛ አቅም የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት፤ “ፍልስጤማዊያን መሬታቸው ሳይሸራረፍ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ” በኤክስ ገጽ ላይ ጽፈዋል፡፡

በዐረብ ሀገራት ጉባዔ ላይ ተቀባይነት ያገኘው የግብጽ ምክረ ሐሳብ፤ በቀጣይ ሣምንት በሚካሔደው የኢስላማዊ ሀገራት ትብብር ድርጅት ስብሰባ ላይ እንደሚጸድቅ ግብጽ አስታውቃለች፡፡ የድርጅቱን ስብሰባ መጋቢት 7/2017 የምታስተናግደው የሳዑዲ ዐረቢያዋ ጂዳ ከተማ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምክረ ሐሳቡ በጂዳ እንዲጸድቅ ተደርጎ የሙስሊሙ እና ዐረብ ሀገራት ዕቅድ እንዲሆን እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular