ፕሬዝዳንት ዐብዱልፈታህ አልሲሲ የሚመሯት ግብጽ፤ የጋዛ አስተዳደር ከሐማስ ተነጥቆ በአዲስ እንዲተካ የጠየቀችበት ምክረ ሐሳብ በዐረብ ሊግ ጉባዔ ላይ የሚቀርበው በዛሬው እለት መሆኑ ተነግሯል፡፡ ሬውተርስ የዜና ወኪል በጋዛ ድርድር ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ሥማቸው እንዲጠቀስ ካልፈቀዱ ባለሥልጣን አግኝቼዋለሁ ባለው በግብጽ የተዘጋጀ ሠነድ ላይ፤ የፍልስጤሙን ሐማስ የሚተካው አስተዳደራዊ ድጋፍ ሰጭ ተልዕኮ “ላልተወሰነ ጊዜ” የሚቆይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ለጋዛ አዲስ ምክረ ሐሳብ ያቀረበችው ግብጽ፤ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይፋ ባደረጉት ጋዛን ከነዋሪዎቿ የማጽዳት እቅድ፤ ፍልስጤማዊያንን ለማስፈር ከታጩት ሀገሮች መካከል አንደኛዋ መሆኗ የሚታወቅ ነው፡፡ አዲሱ ምክረ ሐሣብ ይህን የትራምፕን የጋዛ ነዋሪዎን የማፈናቀል እቅድ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ የሚያደርግ ነው፡፡
በጋዛ የሚመሠረተው አዲስ አስተዳደር የሰብዓዊ ድጋፍ እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን የማስጀመር ኃላፊነት እንደሚወስድ ተጠቅሷል፡፡ የሐማስን ከአስተዳደሩ መነሳት የሚጠይቀው ሠነድ፤ ይህ የማይፈጸም ከሆነ ለመልሶ ግንባታም ሆነ ለሰብዓዊ ድጋፍ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት አዳጋች ሊሆን እንደሚችል ያትታል፡፡ ሠነዱ የጋዛ አስተዳደር ቢመሠረትም የሚመራው በማን እንደሆነ የጠቀሰው ነገር የለም፡፡
በግብጽ የተዘጋጀውን ሠነድ በተመለከተ የዜና ወኪሉ የሐማስ ከፍተኛ አመራር የሆኑትን ሳሚ አቡ ዙሕሪን አናግሬ፤ ስለተጠቀሰው ምክረ ሐሳብ ቡድኑ ምንም እንደማያውቅ ገልጸዋል ብሏል፡፡ አያይዘውም የጋዛ ቀጣይ የሚወሰነው በራሳቸው በፍልስጤማዊያን ብቻ መሆኑን በመናገር፤ ሕዝቡ ያልፈቀደውን የውጭ አስተዳደር ለመጫን የሚደረገውን ማንኛውንም ሙከራ እንደሚቃወም አስረድተዋል፡፡
ሐማስ ይህን ቢልም የዜና ወኪሉ አናገርኳቸው ያላቸው ሌላ ሥማቸው ያልተጠቀሰ የፍልስጤም አስተዳደር ባለሥልጣን፤ በጋዛ ጉዳይ የተለያዩ ፍልስጤማዊያን ባለሞያዎችን ያቀፈ ኮሚቴ የፍልስጤምን አስተዳደር ለስድስት ወራት እንዲያግዝ ከስምምነት ላይ ደርሰናል እንዳሉት አስነብቧል፡፡ ሐማስ ከግብጾች ጋር ተስማምተናል ያለውን በማሕሙድ አባስ የሚመራውን የፍልስጤም አስተዳደር በመተካት ጋዛን ማስተዳደር የጀመረው እ.አ.አ በ2007 እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በግብጽ የተዘጋጀው ሠነድ የጠቀሰው ሌላኛው ጉዳይ፤ ጊዜያዊውን አስተዳደር ለመደገፍ የፈንድ ቦርድ አስተዳደር ማቋቋም እና ለጋሾችን የሚያሳትፍ ኮንፈረንስ በማዘጋጀት ለጋዛ የረዥም ጊዜ መልሶ ግንባታ እና የልማት ዕቅድ መዋጮዎችን መፈለግን የሚመለከተው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ የነዳጅ አምራች ሀገሮቹ ሳዑዲ ዐረቢያ፣ ኳታር እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ከሀገሮቹ መካከል የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ሐማስን ጨምሮ ሌሎች የታጠቁ ኃይሎችን “እንደ ሥጋት ስለምትቆጥር” የሚጠበቀውን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ሐማስ ጋዛን ለቆ እንዲወጣ ጥያቄ ማቅረቧ እንደማይቀር ተገልጿል፡፡
ሬውተርስ አገኘሁት ያለውን ሠነድ በተመለከተ ግብጽም ሆነ ሌሎች የዐረብ እና ሙስሊም ሀገራት ይፋዊ ድጋፍም ሆነ ማስተባበያ አልሰጡም፡፡ በዛሬው እለት ከሚካሄደው የዐረብ ሊግ አስቸኳይ ጉባዔ አስቀድሞ ሳዑዲ ዐረቢያ የግብጽ እና ጆርዳንን ጨምሮ የሰባት ሀገሮችን መሪዎችን ወደ ሪያድ ጠርታ “በወንድማማችነት መንፈሥ ነው የተደረገ ነው” የተባለ ስብሰባ መከናወኑ ይታወሳል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












