በአፋር ክልል ስምንት ንጹሐን የጅቡቲ መንግሥት በታጣቂዎች ላይ ሰንዝሮታል በተባለ ጥቃት ተገድለው፣ ሌሎች ስምንት መቁሰላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል። እንደ ባለሥልጣናት ከሆነ ንጹሐኑ የተገደሉት ሐሙስ ጥር 22/2017 ከሰዓት በኋላ ነው።
ጥቃቱ የተፈፀመው በአውሲ ረሱ ዞን ኤሊዳር ወረዳ ውስጥ በሚገኘው በኪያሩ ቀበሌ ነው። ኪያሩ የተሠኘው ቀበሌ በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ድንበር ላይ የሚገኝ ሥፍራ ነው።
በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል በተፈረመ ስምምነት በድንበሩ በሁለቱም በኩል አምስት ኪሎ ሜትር ራዲየስ ነፃ ቀጣና እንዲሆን የተደረገ ነዥ። የእንግሊዝኛው ዘ ሪፖርተር ጋዜጣ በአካባቢው ከሚገኙ ምንጮች ሰምቻለሁ ብሎ እንደዘገበው፣ ነፃ ቀጣናው በአብዛኛው ከጅቡቲ መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኙ የታጠቁ ቡድኖች የሚርመሰመሱበት ነው።
የኤሊዳር ወረዳ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ሙሐመድ በጥቃቱ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠው፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት በማግሥቱ ጧት ወደ ሥፍራው ባመሩበት ወቅት የከፊሉ ሟቾች የቀብር ሥነ ሥርዐት ሲፈፀም እንደነበር ለጋዜጣው ገልፀዋል። ከተገደሉት መካከል አምስቱ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 20 ይገመታል የተባለ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በ25 እና 30 መሃል እንደሚገመቱ ተጠቁሟል።
የኮሙኒኬሽን ኃላፊው እስካሁን ባሰባሰቡት መረጃ መሠረት ጥቃቱ የተፈፀመው በጅቡቲ መንግሥት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል ብለዋል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌደራል መንግሥት የሰጡት ማብራሪያ የለም።
በጉዳዩ ላይ እስካሁን ከኢትዮጵያ መንግሥት ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም፣ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ የሟቾችን አስከሬን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እና ቪድዮዎች ተሠራጭተዋል። (ሚንበር ቲቪ)
★ ★ ★
Minber TV | EthioSat | 11545 | H | 45000












