የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ በቀጣይ በሚያካሔደው የአመራር ምርጫ ሕዝበ ሙስሊሙ በንቃት እንዲሳተፍ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል። ጠቅላይ ምክር ቤቱ ይህን ጥሪ ያቀረበው በዛሬው ዕለት ካከናወነው ሦስተኛ ዓመት አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በኋላ ባወጣው የአቋም መግለጫ ነው።
ዛሬ ቅዳሜ ጥር 24/2017 ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባው በገለልተኛ የባለሞያዎች ቡድን ተዘጋጅቷል ያለውን የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያና የምርጫ ማስፈፀሚያ መመሪያ ሠነድን መርምሮ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁንም አሳውቋል።
ምርጫው ኢስላማዊ እሴቶችን ጠብቆ በፍትሐዊነት እንዲከናወን ሚናውን በአግባቡ እንደሚወጣ የገለጸው ምክር ቤቱ፣ ከጥቂት ወራት በኋላ ይከናወናል ባለው ምርጫ የሚመረጠው አመራር ተቋሙን ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራ መሆኑን ገልጿል። ምክር ቤቱ ምርጫው በቀጣይ ወራት ይካሔዳል ከማለት ባሻገር ትክክለኛ የጊዜ ሠሌዳውን ይፋ አላደረገም።
በምርጫው ላይ እድሜው የደረሰ ሁሉም ሙስሊም በተዋረድ ያሉ ምክር ቤቶች በሚያዘጋጁት የአፈፃፀም መመሪያ መሠረት በአቅራቢያው በሚገኝ መስጅድ በመመዝገብ የቀጣይ ተወካዮችን ሊመርጥ እንደሚገባም አሳስቧል። ሆኖም በምርጫው ለመሣተፍ የተቀመጠውን ዝቅተኛ የዕድሜ እርከን አልጠቀሰም።
በቀጣይ ወራት ይካሔዳል የተባለው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ የወቅቱ ኃላፊዎች ወደ ሥልጣን የወጡት በሐምሌ 2014 ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ለአመራሮቹ የሰጠው የሥልጣን ጊዜ ሦስት ዓመት ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












