የሶሪያ አዲሱ አመራር የሀገሪቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት በሻር አል አሰድ ተላልፈው እንዲሰጠው ለሩስያ ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል፡፡ ጥያቄው የቀረበው በመሪው አሕመድ አል ሻራ በኩል ነው፡፡
ሬውተርስ የዜና ወኪል ለጉዳዩ ቅርበት ካለው አንድ ምንጭ ሰምቻለሁ ብሎ እንደዘገበው፤ አሕመድ አል ሻራ ጥያቄውን ያቀረቡት ለሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚካኤል ቦግዳቮቭ ነው፡፡ ጥያቄው የቀረበለት የሩስያ መንግሥት ለ25 ዓመታት ሶሪያን የመሩትን በሻር አል አሰድን ካስጠለለ ሁለት ወራት ሊሞላ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ወደ ሩስያ የኮበለሉት፤ አሁን ተላልፈው እንዲሰጧቸው የጠየቁት አሕመድ አል ሻራ የሚመሩት ‘ተሕሪር ሐያ አል ሻም’ የተሰኘው ቡድን ደማስቆን በመቆጣጠሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡
አሰድ በሩስያ ቢጠለሉም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚካኤል ቦግዳቮቭ የተመራ የሀገሪቱ ልዑክ ወደ ደማስቆ በማምራት፤ ከአዲሱ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ማድረጉን የቲአርቲ ዘገባ ያመለክታል፡፡ ወደ ደማስቆ ያቀናውን ልዑክ የመሩት የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦግዳቪቭ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪካ ልዑክ በመሆን ደርበው የሚሠሩ ናቸው፡፡

ከሶሪያ መሪ ጋር ስላደረጉት ውይይት የተናገሩት ልዑኩ፤ ሀገራቸውን የሶሪያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንደምታከብር ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም ከሶሪያ ባለሥልጣናት ጋር ቋሚ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ሀገራቸው ይህን ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቀጣይ የሶሪያ አቻቸው አሰድ ሐሰን አል ሻባኒ፤ ሞስኮን እንዲጎበኙ ግብዣ አቅርበዋል፡፡ እንደ ቲአርቲ ከሆነ የጉብኝት ግብዣው የመጣው የአውሮፓ ኅብረት በሶሪያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማንሳት የውጭ ኃይሎች ከሀገሪቱ መውጣት ጋር እንደሚገናኝ በመግለጽ፤ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ሩሲያ በህሜይሚም እና ታርቱስ የሚገኙትን ወታደራዊ ጣቢያዎቿን እንድትለቅ እንዲጠይቁ ካሳሰበ ቀናት በኋላ ነው።
የሶሪያ አዲስ አስተዳደር በተደጋጋሚ በሀገሪቱ ላይ በአሜሪካ እና አውሮፓ ኅብረት የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












