በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ሙስሊም ተማሪዎች ላይ ሒጃብ ክልከላ የጣሉ አምስት ትምህርት ቤቶች ርእሰ መምሕራን፤ ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የሰጠው የወረዳው ፍርድ ቤት ነው። ፍርድ ቤቱ ርእሰ መምሕራኑ ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የሰጠው ከዚህ ቀደም የሰጠውን እግድ ለማስፈፀም እምቢተኛ ሆነዋል በሚል ነው።
የወረዳ ፍርድ ቤት ይህን ትዕዛዝ ያሳለፈው ዛሬ ሰኞ ጥር 19/2017 በዋለው ችሎት ነው። በፍርድ ቤቱ ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ትምህርት ቤቶች ርእሳነ መምሕራን፤ የ“አክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት”፣ “ወርኢይ”፣ “ክንደያ”፣ “ኣብርሃ ወ ኣጽብሃ” እና “አሉሚናይ” ናቸው፡፡
የወረዳው ፍርድ ቤት ጥር 6/ 2017 ባሳለፈው ውሳኔ በተማሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እግድ የጣሉትን እነዚህን ትምህርት ቤቶች በሥም በመጥቀስ የሒጃብ ክልከላ ለመጣል መነሻ ሆኗል ያሉትን መመሪያው ተግባራዊ እንዳያደርጉ እግድ መጣሉ ይታወሳል። ለትምህርት ቤቶቹ የተላለፈው ትዕዛዝ ለትምህርት ቢሮ ጭምር የተላከ ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሲያሳልፍ በምክንያት ያቀረበው ለጉዳዩ እልባት እስኪሰጠው ድረስ ሒደቱ በተማሪዎቹ ላይ የሚያደርሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ነው፡፡ በዚህም ተማሪዎቹ ሒጃባቸውን ለብሰው ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ትእዛዝ የሰጠ ቢሆንም ትምህርት ቤቶቹ ውሳኔውን ማስፈፀም ሳይችሉ ቀርተዋል።
ክርክሩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ በተማሪዎች ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መቆም አለበት ያለው ፍርድ ቤቱ፤ የመመሪያው ተግባራዊነት ላይ እግድ የተጣለው ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ መሆኑንም አስታውቆ ነበር፡፡ ትምህርት ቤቶቹ ትዕዛዙን ማስፈፀም ባለመቻላቸው የካቲት 6/2017 ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርባቸው ውሳኔ አሳልፏል። የአክሱም ወረዳ ፍርድ ቤት ትምህርት ቤቶቹ ውሳኔውን ማስፈፀም አለመቻላቸው የፍርድ ቤቱን ተቋማዊ አሠራር አለማክበር መሆኑንም ገልጿል።
በከተማው በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚገኙ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሒጃብ አድርገው እንዳይገቡ ክልከላ የተጣለባቸው ከታኅሣሥ 8/2017 አንስቶ ነው። (ሚንበር ቲቪ)












