የሐማስ መሪዎች በፍልስጤም አዲስ የጋራ አስተዳደር በሚመሠረትበት ሁኔታ ላይ ከግብጽ ባለሥልጣናት ጋር የመከሩት፤ በካይሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ ይህን የገለጸው ሰኞ እለት በሙሐመድ ደርዊሽ የተመራ ልዑክ ወደ ከተማዋ ማምራቱ ከተነገረ በኋላ ነው፡፡
ሐማስ ባወጣው መግለጫ እንዳሳወቀው፤ ከግብጽ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሐሰን ረሻድ ጋር ባደረገው ውይይት በተለይም በጋዛ ስለሚመሠረተው ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ተነስቷል፡፡ መሪዎቹ ይህን ውይይት ከማድረጋቸው አስቀድሞ ማሕሙድ አባስ ለሚመሩት ሌላኛው የፍልስጤም ቡድን ፈትሕ የትብብር ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡
ቡድኑ ከግብጽ ባለሥልጣናት ጋር ስለ ጋዛ አዲስ የጋራ አስተዳደር ምክክር ማድረጉን ቢገልጽ፤ ዝርዝር ጉዳዮችን ይፋ አላደረገም፡፡ በውይይቱ ላይ አስር ቀናት ያስቆጠረው የጋዛ ተኩስ አቁም ትግበራ እና የእስረኛ ልውውጥን የተመለከቱ ጉዳየችም በአጀንዳነት መቅረባቸው ተገልጿል፡፡ ከተኩስ አቁም ትግበራው ጋር ተያይዞ የእስራኤል ባለሥልጣናት ስምምነት መጣሳቸውን የሐማስ መሪዎች ተናግረዋል፡፡ አክለውም እስራኤል “ያለምንም ማዘግየት ወይም ማደናቀፍ” የስምምነት ውሎችን እንትፈጽም የማስገደድን አስፈላጊነት መግለጻቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
በተኩስ አቁሙ በ42 ቀናት ውስጥ በአጠቃላይ 2 ሺሕ ገደማ ፍልስጤማዊያን ነጻ ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሐማስ በበኩሉ 33 በሕይወት ያሉ እንዲሁም ሟች የእስራኤል ምርኮኞችን ያስረክባል ተብሏል። እስካሁን ድረስ በእስራኤል ማጎሪያ ቤቶች ውስጥ ይገኙ የነበሩ 290 ፍልስጤማዊያን ነጻ የወጡ ሲሆን፣ ከምርኮቹ መካከል እንዲሁ ሰባቱ ተለቀዋል። ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ነጻ ከወጡት 200 ፍልስጤማዊያን ውስጥ 70 ሰዎች ወደ ግብጽ ተጓጉዘዋል።
ባለፉት 15 ወራት 47 ሺሕ ፍልስጤማዊያንን በመግደል፤ ሺሕዎችን ያፈናቀለ ጥቃት ስትሰነዝር የቆዩ የእስራኤል ባለሥልጣናት፤ በቀጣይ በጋዛ በሚመሠረተው አስተዳደር የሐማስ ተሳትፎ እንዳይኖር እየሠሩ እንደሚገኙ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት ከተገደሉት በተጨማሪ ከ11 ሺሕ በላይ ንጹሐን ደብዛቸው ጠፍቷል፡፡ ለተፈጸመው ጥቃት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ እንዳወጣባቸው ይታወቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












