የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ተማሪዎች በአፋጣኝ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ አስተዳደራዊ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠቅላይ ምክር ቤት ማሳሰቢያ የሰጠው ለትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ምክር ቤቱ በጻፈው ማሳሰቢያ፤ ለሚኒስቴሩ በአንድ ወር ውስጥ ሦስት ደብዳቤ ቢጽፍም ምላሽ እንዳልተሰጠው ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው ዛሬ ሐሙስ ጥር 15/2017 በጻፈው “የመጨረሻ” ባለው ደብዳቤው ነው፡፡ በዚህ ደብዳቤ ላይ በኢስላማዊ አለባበስ ብቻ ሙስሊሞችን ከትምህርት ገበታ ማፈናቀል አካባቢውን እየቀያየረ መቀጠሉን በመግለጽ፤ ከእነዚህ መካከል የዲላ ዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች ከጥር 11/2017 አንስቶ በአለባበሳቸው ምክንያት ትምህርት እንዳይማሩ መደረጋቸውን ጠቅሷል፡፡
ተማሪዎቹ በጨለማ ግቢ ውስጥ እንዳይገቡ ክልከላ እንደተጣለባቸው የገለጸው ምክር ቤቱ፤ ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎቹ በአፋጣኝ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ አስተዳደራዊ ትዕዛዝ በመስጠት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያስቀምጥ ጠይቋል፡፡ “ለመጨረሻ ጊዜ” ቀርቧል ባለው በዚህ ደብዳቤ ላይ አስተዳደራዊ መፍትሔ ካልተሰጠ በቀጣይ የሚወስደው ርምጃ መኖር አልያም አለመኖሩን አልገለጸም፡፡
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ሙስሊም ተማሪዎች በተጣለው የኒቃብ ክልከላ የሚማሩበትን ግቢ ለቀው የወጡት ቅዳሜ ጥር 10/2017 መሆኑን “ሚንበር ቲቪ” ከጀመዓ አሚር እንዲሁም ከሴት ተማሪዎች ማረጋገጥ ችሏል፡፡ እንደ ተማሪዎች ከሆነ፣ ቀድመው ክልከላውን የጣሉት የዩኒቨርሲቲው ሁለት ካምፓሶቸች ናቸው፡፡ እነዚህ ካምፓሶች “ነባሩ ግቢ” እና “ኦዳያ” የተሰኙት የነበሩ ሲሆን፣ ባለፉት ቀናት ቁጥሩ ሠስት ደርሷል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ውስጥ “ከፕሬዝዳንቱ ጋር በተደረገ ስምምነት” ኒቃብ የሚለብሱ ሴት ተማሪዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲማሩ ቆይተዋል የነበረ ቢሆንም ከአንድ ወር ወዲህ ክልከላ እንደተጣለ ተማሪዎች ገልጸዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












