Homeዜናና ወቅታዊዜና“ድምጿ ይሰማ” የተሰኘ የሒጃብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በአዲስ አበባ ሊካሔድ ነው

“ድምጿ ይሰማ” የተሰኘ የሒጃብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በአዲስ አበባ ሊካሔድ ነው

“ድምጿ ይሰማ” የተሰኘ የሒጃብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ በአዲስ አበባ ሊያካሔድ መሆኑን ያስታወቀው የከተማዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ነው፡፡ ዘመቻው የሚጀመረው የፊታችን እሑድ መሆኑን “ሚንበር ቲቪ” ከምክር ቤቱ ኃላፊ ሰምቷል፡፡

የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የሒጃብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ ሊያካሔድ መሆኑን የገለጸው በዛሬው እለት ነው፡፡ የምክር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሪያድ ጀማል ለ“ሚንበር ቲቪ” እንደተናገሩት ከሆነ፤ እሑድ ጥር 18/2017 ይፋ የሚደረገው ንቅናቄ ሒጃብን በተመለከተ የውይይት አጀንዳ የመፍጠር ሚና ይኖረዋል በሚል የሚከናወን ነው፡፡ በዚሁ ቀን የሚጀመረው ንቅናቄ ለአንድ ሳምንት ቆይቶ ጥር 24/2017 (ፌብሩዋሪ 1/2025) በሚከበረው “የዓለም ሒጃብ ቀን” የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡

በንቅናቄው ማስጀመሪያ ቀን በሚኖረው መርሐ ግብር ላይ በሒጃብ ዙርያ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ፡፡ ጽሑፎቹ የሚያጠነጥኑት የሒጃብ ሸሪዓዊ መሠረት፣ ከሕገ መንግሥት እና ሰብዓዊ መብት አንጻር ይሆናል ተብሏል፡፡

ለአንድ ሳምንት ይቆያል በተባለው ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግር ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ መቅረቡን የከተማው ምክር ቤት አስታውቋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ በተጨማሪ ከመስጂዶች፣ ከንግድ ማኅረሰብና ሌሎች በርካታ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤቱ የሒጃብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ የመጣው ባለፉት ቀናት፤ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ በትምህር ቤቶች የተጣለውን የሒጃብ ክልከላ ተከትሎ በመቐለ ከተማ የተቃውሞ ሠልፍ ከተካሔደ በኋላ ነው፡፡ በተቃውሞ ሠልፉ ላይ ከመቐለ እና ዙርያው የተሰባሰቡ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የሙስሊሙ ማኅበሰረብ አባላት በመሳተፍ ድምጻቸውን ያሰሙበት ሆኖ አልፏል፡፡ በተመሣሣይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ዲላ ዩኒቨርሰቲ ከባለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ ተማሪዎች ኒቃብ ለብሰው እንዳይገቡ ክልከላ በመጣሉ ተማሪዎች መማሪያ ግቢ ለቀው መውጣታቸው የሚታወቅ ነው፡፡

እነዚህን ክልከላዎች ያስታወሱት የአዲስ ስአበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሪያድ ጀማል፤ በከተማ ደረጃ ሊካሔድ የታቀደው ንቅናቄ እና የሒጃብ ግንዛቤ ማስጨበጫ “በአንድ አካባቢ ብቻ ባይወሰን” የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ከተማ አቀፍ የሒጃብ ግንዛቤ ንቅናቄ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ በሚገኝበት በአዲስ አበባ ከተማ፤ በጥቅምት ወር 2017 ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ኒቃብ በመልበሳቸው ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ ተደርገው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ ክልከላውን የጣሉት በከተማዋ ውስጥ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ሰባት ትምህርት ቤቶች የነበሩ ቢሆንም “በጊዜያዊነት በተደረገ ንግግር” ተማሪዎቹ በአሁኑ ሰዓት ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የሒጃብ ንቅናቄውን የሚያካሔበት በቀጣይ ሳምንት መጨረሻ ጥር 24 (ፌብሩዋሪ 1/2015) ዓለም አቀፍ የሒጃብ ቀን የሚከበርበት ነው፡፡ ይህ በዓል በ140 የዓለም ሀገራት የሚከበር ነው፡፡ እ.አ.አ በ2013 ናዝማ ኻን በተባለች የባንግላዴሽ የዘር ግንድ ባላት ሙስሊም ሴት በተጀመረው አከባበር፤ ሴቶች ከየትኛውም ሃይማኖትና አመለካከት ቢሆኑ ሒጃብን ለአንድ ቀን ለብሰው ተመክሮ እንዲያገኙ ማድረግ እንዲሁም ሙስሊም ሴቶች ሒጃብን የሚለብሱበትን ምክንያት ማስረዳትና ግንዛቤ ማስፋት ዓላማው ያደረገ ነው።

በተለያዩ አገሮች በተለያዩ መንገዶች በሚከበረው በዓለም አቀፍ የሒጃብ ቀን፤ በመድረክ ዝግጅቶች፣ በፓናል ውይይቶች፣ በጥናታዊ ጽሑፎች፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመቃወም እና የሴቶችን መብት ለማስጠበቅም ጥቅም ላይ ይውላል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular