Homeዜናና ወቅታዊዜናበአክሱም የተጣለውን የሒጃብ ክልከላ የክልሉ አስተዳደር አፋጣኝ እልባት እንዲሰጠው ነእፓ ጠየቀ

በአክሱም የተጣለውን የሒጃብ ክልከላ የክልሉ አስተዳደር አፋጣኝ እልባት እንዲሰጠው ነእፓ ጠየቀ

ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ በሙስሊም ተማሪዎች ላይ የተጣለው የሒጃብ ክልከላ እንዲነሳ የክልሉ አስተዳደር አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስድ የጠየቀው በሊቀመንበሩ ዓብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) ነው፡፡

ሊቀመንበሩ ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርእሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ በጻፉት ደብዳቤ፤ በአክሱም በሙስሊም ተማሪዎች ላይ የተጣለው የሒጃብ ክልከላ “የክልሉንም ሆነ ሌሎች ፍትሕ ወዳድ ዜጎችን እጅግ አሳዝኗል” ብለዋል፡፡ ውሳኔው በተለይ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በሚወስዱ ተማሪዎች ላይ “ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ እና መጻዒ ሕይወታቸውን የሚያጨልም በመሆኑ”፤ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ለችግሩ አፋጣኝ እልባት እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

በአክሱም ከተማ ሴት ተማሪዎች በትምሕርት ቤቶች በተጣለው ሒጃብ ክልከላ ምክንያት ከትምሕርት ገበታ ውጪ የሆኑት ከታኅሣሥ 8/2017 አንስቶ ነው፡፡ የተማሪዎች የሒጃብ ክልከላ በአክሱም ከተማ ጥለውታል የተባሉት ትምህርት ቤቶች፤ “አክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት”፣ “ወርኢይ”፣ “ክንደያ”፣ “ኣብርሃ ወ ኣጽብሃ” እና “አሉሚናይ” መሆናቸው ታውቋል፡፡

ይህን በመቃወም ዛሬ ማክሰኞ ጥር 13/2017 በመቐለ ከተማ ተካሄደ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የጠራው ሠልፍ ተከናውኗል፡፡ ሠልፉ ከማለዳ ጀምሮ የተካሄደው በመቐለ ከተማ ሮማናት አደባባይ ነው፡፡ ሠልፉ የተከናወነው “ሒጃቧንም ትለብሳለች ትምህርቷንም ትማራለች” በሚል መሪ ቃል ነው፡፡ በሠልፉ ከመቐለ እና አካባቢው በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

ሠልፉን በዋነኝነት ያስተባበረው የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በፕሬዝዳንቱ ሸይኽ አደም ዓብዱልቃድር እና ዋና ጸሐፊው ሐጂ ሙሐመድ ካሕሳይ አማካኝነት ከዚህ ቀደም ከትምህርት ቤቶቹ ጋር የነበረው ቢሮክራሲያዊ ሒደት ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ በሂደቱ ለውጥ ባለመምጣቱ የዛሬው የተቃውሞ ሠልፍ እንደተጠራም ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

ከተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ መጠናቀቅ በኋላ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ተወካዮች ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬሬዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ውይይት ማድረጋቸው የታወቀ ሲሆን፣ አቶ ጌታቸው፤ “ሆን ተብሎ አጀንዳ እንዲሆን የተደረገ ነው” ላሉት የሒጃብ ክልከላ፤ በፍጥነት እልባት እንዲሰጠው እናደርጋለን ማለታቸውም ተሰምቷል፡፡

በአክሱም ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሙስሊም ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰው እንዳይማሩ ክልከላ ስለተጣለ፤ በተለይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በትምህርት ሚኒስቴር የሚላከውን የብሔራዊ ፈተና ቅጽ መሙላት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት እንዳወጣው መረጃ ከሆነ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ምዝገባ ጥር 6/2017 ተጠናቋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular