የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በአክሱም በሙስሊም ተማሪዎች ላይ የተጣለውን የሒጃብ ክልከላ በመቃወም በመቐለ በሚካሔደው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ፤ ዕውቅና ያልተሰጣቸው መፈክሮች እና ባነሮችን መያዝ የተከለከለ መሆኑን የገለጸው በዛሬው እለት ነው፡፡ ምክር ቤቱ ዛሬ ሰኞ ጥር 12/2017 በሰጠው መግለጫ ሁሉም ኅብረተሰብ በሠልፉ ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዚህ መግለጫ ላይ፤ በመቐለ ከተማ ሮማናት አደባባይ በሚካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ የሚስተጋቡት መፈክሮች እና የሚውለበለቡ ባነሮች በምክር ቤቱ እውቅና የተሰጣቸው ብቻ መሆኑን በማስታወቅ፤ ከዚህ ውጭ ባሉት ላይ የፀጥታ አካላት ቁጥጥር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የምክር ቤቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ሠልፉን ማድረግ ያስፈለገው በአክሱም ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች አስተዳዳሪዎች በሙስሊም ተማሪዎች ላይ የጣሉትን የሂጃብ ክልከላ እንዲያነሱ በተደጋጋሚ በመደበኛ የደብዳቤ ልውውጥ ሙከራ ቢደረግም በአቋማቸው በመጽናታቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ በትምህርት ቤቶች የተጣለውን የሒጃብ ክልከላ የሚቃወም ሕዝባዊ ሠልፍ በቀጣይ ሳምንት እንደሚካሔድ ያስታወቀው ጥር 8/2017 ነበር። ቀድሞ የተቃውሞ ሠልፉን ለማድረግ ቀጠሮ ተይዞ የነበረው ጁመዓ ጥር 9 የነበረ ቢሆንም የጊዜ ሠሌዳው ከሌላ ሃይማኖታዊ በዓል ጋር በመገጣጠሙ የቀን ለውጥ ተደርጎበት ነገ ማክሰኞ ጥር 13/2017 እንዲካሔድ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም የሒጃብ ክልከላውን በተመለከተ ታኅሣሥ 25/2017 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ጉዳዩ እልባት የማይሰጠው ከሆነ “ወደ ቀጣይ ርምጃ” እንደሚሻገር ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
በአክሱም ከተማ በተማሪዎች ላይ የሒጃብ ክልከላውን ጥለውታል የተባሉት ትምህርት ቤቶች “አክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት”፣ “ወርኢይ”፣ “ክንደያ”፣ “ኣብርሃ ወ ኣጽብሃ” እና “አሉሚናይ” ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












