ባለፈው ሳምንት የተደረሰው የሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ፤ በእስራኤል ማጎሪያ ቤቶች ይገኙ የነበሩ ዘጠና ፍልስጤማዊያን ነጻ መውጣታቸው ታውቋል፡፡ ፍልስጤማዊያኑ ነጻ የወጡት ሐማስ በምርኮ ከያዛቸው ሠፋሪ እስራኤላዊያን ውስጥ ሦስቱን ከለቀቀ በኋላ ነው፡፡
ለፍልስጤማዊያኑ ነጻ መውጣት ምክንያት የሆነው የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት፤ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ትናንት እሑድ ማለዳ 12፡30 ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሚለቀቁት ምርኮኞች ሥም ዝርዝር ካልተሰጠኝ ተኩስ ማቆም አንችልም በማለት በወታደሮቹ ጥቃቱን ቀጥሏል፡፡
ለሰዓታት ዘግይቶ ተግባራዊ የተደረገው የተኩስ አቁም ተግባራዊ ተደርጎ፤ አመሻሹን በሐማስ ቁጥጥር ስር የነበሩ ሦስት ምርኮኞች ከተለቀቁ ሰባት ሰዓታት በኋላ ፍልስጤማዊያኑ ተሰባስበው ከነበሩበት ኦፌር ወሕኒ ቤት በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ባልደረቦች አማካኝነት እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡
ነጻ ከወጡት መካከል 78 ፍልስጤማዊያን እስራኤል በወረራ ከያዘችው ዌስት ባንክ የተያዙ መሆናቸውን ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡ ፍልስጤማዊያኑ ወደ ቀያቸው ሲመለሱ የእስራኤል ወታደሮች ከዚህ ቀደም ያደርጉ እንደነበረው ቤተሰቦቻቸው ደስታ ከመግለጽ እንዲቆጠቡ ሲከለክሉ ታይተዋል፡፡ በተጨማሪም ወታደሮቹ እያንዳንዱ ተፈቺ ፍልስጤማዊ መኖሪያ ቤት ላይ ሲያንዣብቡ ነበር ተብሏል፡፡
ፍልስጤማዊያኑ የተለቀቁት በሦስት ዙር ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ተኩስ አቁም በቀዳሚው ስምምነት መሠረት ነው፡፡ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ ቢያንስ 1 ሺሕ ፍልስጤማዊያን ነጻ ይወጣሉ ይጠበቃል፡፡ በስምምነቱ ሐማስ 33 ምርኮኞችን ይለቃል የተባለ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ምርኮኛ 30 ፍልስጤማዊያን የሚለቀቁ ይሆናል፡፡
በትናንትናው እለት ነጻ ከወጡት ውስጥ አንድ ፖለቲከኛ እንዲሁም ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር የታሰረችው ጋዜጠኛ ቡሽራ አል ጠዊል ተካተዋል፡፡ የመፈታት ሒደቱን በተመለከተ ለአልጀዚራ የተናገረችው ጋዜጠኛዋ፤ ሌሊት 9 ሰዓት ከነበረችበት ወሕኒ ቤት እንድትነሳ ተደርጎ ወደ ኦፌር መዛወራቸውን አስረድታለች፡፡ ሒደቱ ፈታኝ እንደነበር በማስታወስ፤ በመጨረሻ ነጻ በመውጣቷ መደሰቷ ገልጻለች፡፡ ጋዜጠኛ ቡሽራ ከእስር ነጻ ብትወጣም ወልጅ አባቷ አሁንም በወሕኒ እንደሚገኙ ተናግራለች፡፡ ጥቂት እፎይታ የሰጣት ግን በቀጣይ ይፈታሉ መባሉ እንደሆነም አክላለች፡፡

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከመደረጉ አስቀድሞ በነበሩት አስራ አምስት ወራት የእስራኤል ወታደሮች በሰነዘሩት ጥቃተ ከ46 ሺሕ በላይ ፍልስጤማዊያን ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል፡፡ ከተገደሉት በተጨማሪ 90 በመቶ የጋዛ ነዋሪ ለመፈናቀል ተገዷል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












