በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ውስጥ የሚገኘው ዲላ ዩኒቨርሰቲ በጣለው የኒቃብ ክልከላ፤ ሙስሊም ተማሪዎች የሚማሩበትን ግቢ ጥለው መውጣታቸውን ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናገሩ፡፡ ተማሪዎች በአሁኑ ሰዓት በዲላ ከተማ መስጂድ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ሙስሊም ተማሪዎች በተጣለው የኒቃብ ክልከላ የሚማሩበትን ግቢ ለቀው የወጡት ቅዳሜ ጥር 10/2017 መሆኑን “ሚንበር ቲቪ” ከጀመዓ አሚር እንዲሁም ከሴት ተማሪዎች ማረጋገጥ ችሏል፡፡ እንደ ተማሪዎች ከሆነ፣ ክልከላውን የጣሉት የዩኒቨርሲቲው ሁለት ካምፓሶቸች ናቸው፡፡ እነዚህ ካምፓሶች “ነባሩ ግቢ” እና “ኦዳያ” የተሰኙት መሆናቸው ታውቋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ውስጥ “ከፕሬዝዳንቱ ጋር በተደረገ ስምምነት” ኒቃብ የሚለብሱ ሴት ተማሪዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲማሩ ቆይተዋል ተብሏል፡፡ ክለከላ መደረግ ከጀመረ አንድ ወር እንዳስቆጠረ የሚናገሩት ተማሪዎቹ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ዩኒቨርሲቲው ክልከላ ቢያደረግም በንግግር ሒደት ውስጥ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን የክልከላውን ምክንያት ለማወቅ የቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጠው በትናንትናው እለት ሙሉ ለሙሉ ግቢ ውስጥ እንዳይገቡ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ የሙስሊም ተማሪዎች ኅብረት ለዞኑ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በደብዳቤ እንዳሳወቀ ታውቋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ምክር ቤቱ ጥር 5/2017 ለዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ፤ የተጣለው ክልከላ ተገቢ እንዳልሆነ በማሳወቅ ተቃውሞውን አቅርቧል፡፡ “ሚንበር ቲቪ” በተመለከተው በዚህ ደብዳቤ ላይ አለባበስን በተመለከተ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ጉባዔ ባለፈው ታኅሣሥ ወር በሰጠው ፈትዋ (ብይን) “ማንኛውም አካል ወይም ግለሰብ” የፈጣሪ ትዕዛዝ የሆነውን አለባበስ “መከልከልም ሆነ ማደናቀፍ” እንደሌለበት ማሳሰቢያ መስጠቱን በማስታወስ ተማሪዎች የተወጡት ኢስላማዊ ግዴታ መሆኑን ጠቁሟል።
በተጨማሪም የከፍተኛ ተማሪዎች የዲሲፕሊን መመሪያ፤ በዩኒቨርሲቲ ቅጽር ግቢ የተከለከሉ ተግባራትን በሚዘረዝርበት ጊዜ “ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ መልዕክት ያላቸውን አልባሳት፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ ጌጣጌጥ፣ የተለያዩ ቦርሳዎችና መያዣዎችን መጠቀም” የሚለውን ከማንኛውም ሃይማኖታዊ አለባበስ ጋር ማያያዝ፤ “የብሔር ወይም የሃይማኖት ማንነትን ሳያወልቁ የትምህርት ቅጽር ግቢ ውስጥ መግባት አይቻልም እንደማለት” መሆኑንም አብራርቷል፡፡
አያይዞም የተከለከሉ አለባበሶች ዝርዝር ውስጥም ቢሆን የሙስሊም ሴቶች ኢስላማዊ አለባበስ እንደሌለ የመመሪያውን አንቀጽ 7 ቁጥር 17.2ን ጠቅሷል፡፡ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት መካከል “የተቦጫጨቀ፣ ገላን የሚያሳይ ልብስ በማድረግ የውስጥ ቁምጣን ማሳየት፣ ከጉልበት በላይ ያጠረ ቀሚስ መልበስ” ይገኙበታል፡፡ የምክር ቤቱ ደብዳቤ በግልባጭ ለደቡብ ኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ ለዲላ ከተማ ሠላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤትና ለሌሎችም ባለድርሻ አካላት እንዲደርስ መደረጉንም የሚያሳይ ነው፡፡
የዞኑን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ደብዳቤ ተከትሎ፤ የዲላ ዩኒቨርሰቲ ፕሬዝዳንት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ፍቃደኛ እንደሆኑ ገልጸው የነበረ ቢሆንም፤ ለዛሬ እሑድ ጥር 11/2017 የተያዘው ቀጠሮ በራሳቸው በድጋሚ እንደተሰረዘ ለ“ሚንበር ቲቪ” የተናገሩ የደቡብ ኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ አረጋግጠዋል፡፡ ዲላ ዩኒቨርሰቲ በጣለው የኒቃብ ክልከላ ምክንያት ትምህርት ለማቋረጥ ከተገደዱት መካከል በነገው እለት ለፈተና መቀመጥ ያላባቸው መኖራቸው ታውቋል፡፡ ሆኖም ጉዳዩ እልባት ባለማግኘቱ ፈተናውን መቀመጥ አንችልም የሚል ሥጋት ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡












