Homeዜናና ወቅታዊዜናየትምህርት ቢሮን አዲስ ውሳኔ ተከትሎ ወደ ትምህርት ቤት ያመሩ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች...

የትምህርት ቢሮን አዲስ ውሳኔ ተከትሎ ወደ ትምህርት ቤት ያመሩ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ዳግም ከበር እንዲመለሱ መደረጋቸውን ተናገሩ

በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የሚገኙ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች የትምህርት ቢሮን አዲስ ውሳኔ ተከትሎ ወደ ትምህርት ቤት ቢያመሩም፤ ወደ ቅጽ ግቢ መግባት ስላልተፈቀደላቸው ዳግም ከበር እንዲመለሱ መደረጋቸውን ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሐሙስ ጥር 8/2017 ለአክሱም ከተማ ትምህርት ቢሮ የተማሪዎችን አለባበስ በተመለከተ በጻፈው ደብዳቤ ከትምህርት ገበታ ውጪ የተደረጉ ተማሪዎች ቀድሞ የነበረውን አለባበስ ተጠቅመው ትምህርት እንዲቀጥሉ ውሳኔ አሳልፎ ነበር። ነገር ግን ምንም ዐይነት ውሳኔ አልደረሰንም ያሉ የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች ዛሬ ጁመዐ ጥር 9/2017 ሒጃብ የለበሱ ሙስሊም ተማሪዎችን እንዲመለሱ አድርገዋል ተብሏል፡፡

በአክሱም የክልሉ ትምህርት ቢሮ ታኅሣሥ 22/2017 ለአክሱም ትምህርት ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ አለባበስን በተመለከተ አዲስ መመሪያም ሆነ እግድ እንደማይቀበል ገልጾ በነባሩ አሠራር እንዲቀጥሉ ማሳሰቢያተሰጥቶ ወደ ትምህርት ቤት ቢያመሩም እንዲመለሱ ተደርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ዳግም ክልከላ የጣሉ ትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች ቢሮው በጻፈው ደብዳቤ ሒጃብ መፈቀዱን በግልጽ አላሠፈረም የሚል ምክንያት ጠቅሰዋል።

በአክሱም ከተማ ሴት ተማሪዎች በትምሕርት ቤቶች በተጣለው ሒጃብ ክልከላ ምክንያት ከትምሕርት ገበታ ውጪ የሆኑት ከታኅሣሥ 8/2017 አንስቶ ነው፡፡

የተጣለውን የሒጃብ ክልከላ ሲቃወም የቆየው የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በቀጣይ ሳምንት ሠልፍ እንደሚካሔድ አስታውቋል፡፡ ምክር ቤቱ ሠልፉ የሚካሔደው ማክሰኞ ጥር 13/2017 እንደሚሆን ሐሙስ ጥር 8/2017 ይፋ አድርጓል፡፡

በከተማው በተማሪዎች ላይ የሒጃብ ክልከላውን ጥለውታል የተባሉት ትምህርት ቤቶች “አክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት”፣ “ወርኢይ”፣ “ክንደያ”፣ “ኣብርሃ ወ ኣጽብሃ” እና “አሉሚናይ” መሆናቸው ታውቋል፡፡  ሙስሊም ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰው እንዳይማሩ ክልከላ ስለተጣለ፤ ለሀገር አቀፍ ፈተና የሚቀመጡ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በትምህርት ሚኒስቴር የሚላከውን የብሔራዊ ፈተና ቅጽ መሙላት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት እንዳወጣው መረጃ ከሆነ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ምዝገባ ጥር 6/2017 አመሻሽ ላይ ተጠናቋል፡፡ በአክሱም የሚገኙ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ በመደረጋቸው ቅጹን እንዳልሞሉ “ሚንበር ቲቪ” ማረጋገጥ ችሏል፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular