Homeዜናና ወቅታዊዜናበአክሱም የተማሪዎችን የሒጃብ ክልከላ የሚቃወም ሠልፍ በቀጣይ ሳምንት ሊካሔድ ነው

በአክሱም የተማሪዎችን የሒጃብ ክልከላ የሚቃወም ሠልፍ በቀጣይ ሳምንት ሊካሔድ ነው

በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ በትምህርት ቤቶች የተጣለውን የሒጃብ ክልከላ የሚቃወም ሕዝባዊ ሠልፍ በቀጣይ ሳምንት እንደሚካሔድ ያስታወቀው የክልል እስልምና ጉዳዮ ከፍተኛ ምክር ቤት ነው፡፡ ምክር ቤቱ ሠልፉ የሚካሔደው ማክሰኞ ጥር 13/2017 እንደሚሆን ይፋ አድርጓል፡፡

የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ይህን ያስታወቀው ዛሬ ሐሙስ ጥር 8/2017 ባወጣው አጭር ማስታወሻ ነው፡፡ በዚህ ማስታወሻ መሠረት ቀድሞ የተቃውሞ ሠልፉን ለማድረግ ቀጠሮ የተያዘው ነገ ጁመዓ ጥር 9/2017 ነበር፡፡ ሆኖም የተያዘው የጊዜ ሠሌዳ ከሃይማኖታዊ በዓል ጋር በመገጣጠሙ የቀን ለውጥ ተደርጎ ለቀጣይ ሳምንት መዛወሩን ገልጿል፡፡

በተቃውሞ ሠልፉ ላይ ሁሉም ማኅረሰብ እንዲሳተፍ ጥሪ ያቀረበው ምክር ቤቱ፤ ዝርዝር ጉዳዮችን በቀጣይ እንደሚገለጽም ጠቁሟል፡፡

“ሚንበር ቲቪ” ለጉዳዩ ቅርበት ካለው ምንጭ እንደሰማው ከሆነ፤ የተቃውሞ ሠልፉ የሚከናወነው በክልሉ መቀመጫ መቐለ ከተማ ነው፡፡ ሠልፉን የጠራው ምክር ቤቱ፤ ከዚህ ቀደም የሒጃብ ክልከላውን በተመለከተ ታኅሣሥ 25/2017 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ጉዳዩ እልባት የማይሰጠው ከሆነ “ወደ ቀጣይ ርምጃ” እንደሚሻገር ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ይህንኑ በተመለከተም ባለፉት ቀናት በዚሁ ጉዳይ ምክክር ሲያደርግ እንደቆየ ታውቋል፡፡

በከተማው በተማሪዎች ላይ የሒጃብ ክልከላውን ጥለውታል የተባሉት ትምህርት ቤቶች “አክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት”፣ “ወርኢይ”፣ “ክንደያ”፣ “ኣብርሃ ወ ኣጽብሃ” እና “አሉሚናይ” ናቸው፡፡ የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰው እንዳይማሩ አስተዳደራዊ እግድ በጣሉ አምስት ትምህርት ቤቶችና በትምህርት ቢሮ ላይ ክስ መሥርቶ የወረዳው ፍርድ ቤት ማክሰኞ ጥር 6/2017 ተማሪዎች ላይ ክልከላውን የጣሉ አራት ትምህርት ቤቶችን በሥም በመጥቀስ መመሪያውን ተግባራዊ እንዳያደርጉ እግድ ጥሏል። ለትምህርት ቤቶቹ የተላለፈው የእግድ ትዕዛዝ ለትምህርት ቢሮ ጭምር የተላከ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ሒጃብ መልበስ የሚከለክለው መመሪያ ላይ የእገዳ ውሳኔ ቢያሳልፍም ሙስሊም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ እንዳልቻሉ ታውቋል፡፡ በአክሱም ከተማ የሚገኙ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ቅጽ ሳይሞሉ የተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳም ከሁለት ቀናት በፊት ተጠናቋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular