ባለፉት ቀናት ሊቋጭ ከጫፍ ደርሷል በሚል በተደጋጋሚ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሲስተጋባ የነበረው የሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር፤ በመጨረሻ ፍሬ ያፈራ መስሏል፡፡ ትናንት ረቡዕ ጥር 7/2017 ምሽት ላይ ቀድሞ ዜናውን ለዓለም ያደረሰው አልጀዚራ ዐረቢኛ፤ ሐማስ በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ መስማማቱን ገልጿል፡፡
በኳታር ዶሐ ከተማ በዋነኝነት በሽምግልናው አስተናጋጅ ኳታር እና ግብጽ የተመራው ድርድር የአሜሪካ ተወካዮችንም ያሳተፈ ነበር፡፡ አሜሪካ በመጨረሻው የድርድር ምዕራፍ ላይ ያሳተፈችው የፊታችን ሰኞ ሥልጣናቸውን የሚያስረክቡትን የወቅቱን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የመካከለኛው ምሥራቅ ልዑክ እና የተመራጩን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተወካይን ነው፡፡ በዶሐ የሐማስን ልዑክ እየመሩ ስምምነቱን ያስፈጸሙት ኸሊል አል ሐያ ናቸው፡፡

ኸሊል አል ሐያ ስምምነቱን መቀበላቸውን ማረጋገጫ ከሰጡ በኋላ ሲጠበቅ የነበረው ድርድር ፍሬ እንዳፈራ ይፋ የተደረገው በጋዜጠኞች ሲጠበቁ በነበሩት በኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሐመድ ቢን ዓብዱረሕማን ቢን ጃሲም አል ሳኒ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ “ድርድሩ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል” ብለዋል፡፡ እንደ ሸይኽ ሙሐመድ ከሆነ፤ ስምምነቱ ከፊታችን እሑድ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡
ሦስት ዙር ባለው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት በእስራኤል ወሕኒ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ 2 ሺሕ ንጹሐን ፍልስጤማዊያን ነጻ የሚወጡ ይሆናል፡፡ በምትኩ በሐማስ ስር የሚገኙ 33 ምርኮኞችም ይለቀቃሉ፡፡ በተጨማሪም የእስራኤል ጦር ከምሥራቃዊ የጋዛ ክፍል እንደሚወጣ እና የተፈናቀሉ ሰዎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጿል። በግብጽ ድንበር በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የርዳታ ተሽከርካሪዎችም ወደ ጋዛ እንዲገቡ ይፈቀዳል። ከ16 ቀናት በኋላ በሚተገበረው ሁለተኛው የስምምነቱ ዙር ተጨማሪ ምርኮኞች የሚለቀቁበት ይሆናል፡፡ የስምምነቱ የመጨረሻው ዙር ዓመታት ይወስዳል የተባለው ጋዛን መልሶ መገንባት ላይ የሚያተኩር ነው።
ከስምምነቱ ይፋ መደረግ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን የተናገሩት የሐማሱ ከፍተኛ አመራር ኸሊል አል ሐያ፤ ስምምነቱ “የእስራኤል ወረራ መቼም ቢሆን የሕዝባችንን ተጋድሎ እንደማይሰብረው ያረጋገጠ ነው” ብለዋል፡፡ በሒደቱ የተሰዉትን ሁሉ ለአፍታም ቢሆን አንረሳም ያሉት አል ሐያ፤ “በደሉን አንረሳም፤ ይቅርታም አናደርግም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በድርድር ሒደቱ ላይ ተሳትፎ የነበራት አሜሪካ በተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና በተመራጩ ዶናልድ ትራምፕ አማካኝነት መግለጫ ሰጥታለች፡፡ ተሰናባቹ ጆ ባይደን፤ ምክትላቸውን ካማላ ሐሪስን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶንዮ ብሊንከንን አስከትለው መግለጫ የሰጡት፤ የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር መግለጫ ከመጠናቀቁ ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ ነበር፡፡ በድርድሩ ሒደት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ያቀረቡት የተኩስ አቁም ስምምነት በሐማስ ተቀባይነት አግኝቶላቸው የነበሩት ባይደን፤ በንግግራቸው ይህን ባይጠቅሱም በድርድር ሒደቱ ላይ የነበራቸውን ሚና ጎላ በማድረግ ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ይህ ስምምነት የመጣው በምርጫ ያስመዘገብነውን ድል ተከትሎ ነው ሲሉ ራሳቸው በባለቤነት በሚያስተዳድሩት ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ “ሐአሬትዝ” የተሰኘው የእስራኤል ጋዜጣ፤ በድርድር ሒደቱ ትራምፕ የእስራኤል ባለሥልጣናት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ማሳደራቸውን አስነብቧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝም ከስምምነቱ በኋላ ከተናገሩት መካከል ይገኙበታል፡፡ የርዳታ አቅርቦት ጉዳይን በተለየ ሁኔታ ያነሱት ጉቴሬዝ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለስምምነቱ ትግበራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ስምምነቱ ይፋ ሊደረግ መሆኑ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጭምጭምታ ከመሰማቱ አንስቶ በጋዛ የተለያዩ ተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ፍልስጤማዊያን ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል፡፡ ደስታቸውን ሲገልጹ ከነበሩት መካከል የሆነችው በኑሰይራት የተፈናቃይ መጠለያ ውስጥ የምትኖረው ራንዳ ሰሚህ ለአልጀዚራ፡- “ከዓመት በላይ የቆየው ይህ ቅዠት በመጨረሻ ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ መሆኑን ማመን አልቻልኩም። ብዙ ሰዎችን አጥተናል፣ ብዙ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነገር አጥተናል፡፡ ብዙ ረፍት ያስፈልገናል። የተኩስ አቁሙ ሲጀመር የተገደለውን ወንድሜንና የቤተሰቡን አባላት ለመዘየር ወደ ቀብር መሄድ አለብን። አካላቸው በዴይር አል ባላ የመቃብር ሥፍራ ያረፈው እንዲሁ ነው፡፡ ሥፍራውን አስተካክለን፤ ሥማቸውንም በመቃብሩ መጻፍ ይኖርብናል” ብላለች፡፡
ከሐማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት የደረሱ የእስራኤል ባለሥልጣናት ባለፉት 15 ወራት ቢያንስ አርባ ስድስት ሺሕ ፍልስጤማዊያንን ገድለዋል፡፡ ግድያው የተኩስ አቁም ስምምነቱ በተደረሰበት ትናንት ረቡዕ ምሽትም ሳይቆም 80 ንጹሐን ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












