በትግራይ ክልል የሚገኘው የአክሱም ወረዳ ፍርድ ቤት፤ ሒጃብ መልበስ የሚከለክለው መመሪያ ላይ የእገዳ ውሳኔ ቢያሳልፍም ሙስሊም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ እንዳልቻሉ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናገሩ፡፡ በአክሱም ከተማ የሚገኙ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ቅጽ ሳይሞሉ የተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ ተጠናቋል፡፡
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የመጣው የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰው እንዳይማሩ አስተዳደራዊ እግድ በጣሉ አምስት ትምህርት ቤቶችና በትምህርት ቢሮ ላይ ክስ ከመሠረተ በኋላ ነው፡፡
በከተማው በተማሪዎች ላይ የሒጃብ ክልከላውን ጥለውታል የተባሉት ትምህርት ቤቶች “አክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት”፣ “ወርኢይ”፣ “ክንደያ”፣ “ኣብርሃ ወ ኣጽብሃ” እና “አሉሚናይ” መሆናቸው ታውቋል፡፡ የወረዳው ፍርድ ቤት ማክሰኞ ጥር 6/ 2017 ባሳለፈው ውሳኔ በተማሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እግድ የጣሉት አራት ትምህርት ቤቶችን በሥም በመጥቀስ መመሪያውን ተግባራዊ እንዳያደርጉ እግድ ጥሏል። ለትምህርት ቤቶቹ የተላለፈው ትዕዛዝ ለትምህርት ቢሮ ጭምር የተላከ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሲያሳልፍ በምክንያት ያቀረበው ለጉዳዩ እልባት እስኪሰጠው ድረስ ጉዳዩ በተማሪዎቹ ላይ የሚያደርሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ነው፡፡ በዚህም ተማሪዎቹ ሒጃባቸውን ለብሰው ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ትእዛዝ ሰጥቷል። ክርክሩ እልባት እሰኪያገኝ ድረስ በተማሪዎች ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መቆም አለበት ያለው ፍርድ ቤቱ፤ የመመሪያው ተግባራዊነት ላይ እግድ የተጣለው ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ውሳኔው በሒጃብ ምክንያት ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ ያደረጉ ትምህርት ቤቶች ጥር 16/2017 ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ ትእዛዝ የተላለፈበት ነው፡፡ ይህንኑ ውሳኔ ተከትሎ ዛሬ ረቡዕ ጥር 7/2017 ሙስሊም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶች አምርተው እንደነበር ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ወደ ግቢ መግባት ሳይችሉ መመለሳቸውን ለደኅንነቷ ሲባል ሥሟ ያልተጠቀሰ ተማሪ አስረድታለች፡፡ የትምህርት ቤቶች አስተዳደር ለዳግም ክልከላው የፍርድ ቤት ትዕዣዝ በጽሑፍ አልደረሰኝም ማለቱንም ተናግራለች፡፡
በአክሱም ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሙስሊም ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰው እንዳይማሩ ክልከላ ስለተጣለ፤ በተለይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በትምህርት ሚኒስቴር የሚላከውን የብሔራዊ ፈተና ቅጽ መሙላት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት እንዳወጣው መረጃ ከሆነ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ምዝገባ ማክሰኞ ጥር 6/2017 አመሻሽ ላይ ተጠናቋል፡፡ በአክሱም የሚገኙ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ በመደረጋቸው ቅጹን እንዳልሞሉ ሚንበር ቲቪ ማረጋገጥ ችሏል፡፡
የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በክልሉ አክሱም ከተማ በሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ የተጣለው የሒጃብ ክልከላ እልባት የማይሰጠው ከሆነ ወደ ቀጣይ ርምጃ እንደሚሻገር ከዚህ ቀደም ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ የክልሉ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ባለፉት ቀናት በዚሁ ጉዳይ ምክክር ሲያደርግ እንደቆየም “ሚንበር ቲቪ” ተረድቷል፡፡ ሆኖም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ትምህርት ቤቶቹ ስለጣሉት ዳግም ክልከላ እስካሁን ድረስ ያለው ነገር የለም፡፡












