Homeዜናና ወቅታዊዜናከእስራኤል ጋር በሚደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር ላይ “መጠነኛ ለውጥ” መታየቱን አንድ...

ከእስራኤል ጋር በሚደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር ላይ “መጠነኛ ለውጥ” መታየቱን አንድ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ገለጹ

የፍልስጤሙ ሐማስ ከእስራኤል ጋር በሚያደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር “መጠነኛ ለውጥ” መታየቱን የገለጹት ሥማቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ የቡድኑ ከፍተኛ ባለሥልጣን ናቸው፡፡ ሬውተርስ የዜና ወኪል አናግሬያቸዋለሁ ያላቸው እኒህ ባለሥልጣን፤ የስምምነቱ የመጨረሻ ረቂቅ ለሁሉም አካላት መቅረቡንም ጠቁመዋል፡፡

የሐማሱ ከፍተኛ ባለሥልጣን በተኩስ አቁም ድርድሩ ላይ መጠነኛ ለውጥ ተመዝግቧል የሚል አስተያየት የመጣው፤ አሜሪካ፣ ግብጽ እና ኳታር የሚያሸማግሉት የዶሐ ድርድር መቀጠሉ ከተነገረ በኋላ ነው፡፡ ስለ ድርድሩ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በሦስቱ አሸማጋይ ሀገራት ተወካዮች የሚመራው ድርድር በዶሐ ከተማ በአንድ ሕንጻ ውስጥ “በተናጠል” የሚደረግ ነው፡፡ የሐማስ ባለሥልጣን ለመገናኛ ብዙኃን የተናገሩትም፤ ተወካዮቹ ከኳታር አሚር ሸይኽ ተሚም ቢን ሐማድ ቢን ኸሊፋ አልሳኒ ጋር ውይይት አድርገው ሲያጠናቅቁ ነው፡፡ ነገር ግን ሐማስ በድርድሩ ላይ ለውጥ መታየቱን ከመግለጽ ውጪ የሚጠናቀቅበትን ጊዜ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም፡፡  

በሁለቱ አካላት መካከል የተደረገው የመጀመሪያው ዙር የተናጠል ድርድር ስድስት ሰዓታት የፈጀ እንደነበር ቢቢሲ አንድ የፍልስጤም ባለሥልጣን ነግረውኛል ብሏል፡፡ ዛሬ ማክሰኞ ይቀጥላል የተባለው ድርድር፤ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የሚደረግበትና በርካታ ሰዓታት ሊወስድ የሚችል መሆኑም ተገልጿል፡፡

በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ ከስምምነት የሚደረስ ከሆነ የእስራኤል ወታደሮች በወረራ የያዙትን የፍልስጤም መሬት ለቅቀው መውጣት ይጀምራሉ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ሐማስ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ በቁጥጥሩ ስር የሚገኙ ሦስት ምርኮኞችን የሚለቅ ይሆናል፡፡ በሰባተኛው ቀን ደግሞ የሚለቀቁት ምርኮኞች ቁጥር በአራት ይጨምራል፡፡ ሐማስ ይህ ሲያደርግ በእስራኤል ጥቃት የተፈናቀሉ ፍልስጤማዊያን  ከሚገኙበት ከደቡባዊ ክፍል ወደ ሰሜን እንዲመለሱ ይደረጋል፡፡

በተጨማሪም እስራኤል በወሕኒ ቤቶቿ የሚገኙ አንድ ሺሕ ፍልስጤማዊያንን ለመፍታት ተስማምታለች፡፡ ከፍልስጤማዊያኑ መካከል 190 ሰዎች 15 ዓመት እና ከዚያ በላይ የተፈረደባቸው ናቸው ተብሏል፡፡ እስራኤል እነዚህን ፍልስጤማዊያን በነጻ ስትፈታ ሐማስ በአጠቃላይ 34 ምርኮኞችን የሚለቅ ይሆናል፡፡ የመጀመሪያው ዙር ስምምነት ተግባራዊ በተደረገ በ16ኛው ቀን ሁለተኛው ዙር የተኩስ አቁም ድርድር ይጀመራል፡፡

ድርድሩን በመለከተ አንደኛዋ አሸማጋይ አሜሪካ፤ ሊሰናበቱ ጥቂት ቀናት በቀራቸው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዲሁም በተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካኝነት የደረሰበትን ደረጃ ይፋ አድርጋለች፡፡ ጆ ባይደን ባደረጉት ንግግር፤ “በአንዳንድ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የተደረገው ድርድር ለውጥ አሳይቷል፤ ቀሪ ጉዳዮችን በቅርቡ ለማጠናቀቅ እየሠራን እንገኛለን” ብለዋል፡፡

በተመሣሣይ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የሐማስ እና እስራኤል ድርድር “ሊቋጭ ጫፍ ላይ ደርሷል” ሲሉ ለኒውስማክስ ተናግረዋል፡፡ ‘ከስምምነት ላይ ካልተደረሰ የሚከተለው ጥፋት አደገኛ ነው’ በሚል ማስፈራሪያ አዘል መልዕክት ያስተላለፉት ተመራጩ ፕሬዝዳንት፤ የሁለቱ አካላት ድርድር በዚህ ሳምንት “በእጅ መጨባበጥ ይቋጫል” የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በዛሬው እለት ይካሄዳል በተባለው ድርድር ላይ የሁለቱም ፕሬዝዳንት ተወካዮች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡ በመጨረሻው ድርድር ላይ ይሳተፋሉ ያላቸው የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የመካከለኛው ምሥራቅ ተወካይ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የባይደን ተወካይ ብሬት ማግኩርክ ናቸው፡፡

ከሐማስ ጋር ለድርድር የተቀመጡ እስራኤል ባለሥልጣናት፤ ባለፉት አስራ አራት ወራት ቢያንስ 46 ሺሕ ፍልስጤማዊያንን መግደላቸው የሚታወቅ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular