የቀድሞውን የበሻል አል አሰድ አገዛዝ በመገርሰስ ሥልጣን የተቆጣጠሩት የሶሪያ አዲሱ መሪ አሕመድ አል ሻራ፤ “ይቅር ባይነት እና ምሕረት ማድረግ” ለሀገሪቱ ቀጣይ ሕልውና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መሪው የሶሪያ ሕዝብ “ከበቀል እና አብዮት ከሚፈጥረው የመሸበር ሥሜት” መውጣት አለበት ብለዋል፡፡
አሕመድ አል ሸራ ይህን የተናገሩት ጆ ሀጠብ ከተባለ የዘጋቢ ፊልም አዘጋጅ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው፡፡ የ15 ደቂቃ ርዝማኔ በነበረው ቃለ ምልልስ ላይ “የአብዮተኝነት አስተሳሰብ ሀገር አይገነባም” ሲሉ የተደመጡት አል ሻራ፤ ከዚህ ስሜት የመውጣትን አስፈላጊነትን በማንሳትም ተከራክረዋል፡፡ በዚህ ቆይታ ለሕዝባቸውም “አብዮቱ አብቅቷል” የሚል መልዕክት አስላልፈዋል፡፡
ሶሪያ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት አገዛዝ መውደቅ ተከትሎ አሕመድ አል ሻራ በሚመሩት “ሐያት ተሕሪር አል ሻም” በተሰኘው ቡድን ቁጥጥር ስር ከዋለች አንድ ወር ተቆጥሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ቡድኑ አሜሪካ እና ቱርክን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ የመካከለለኛው ምሥራቅ እና ጎረቤት ሀገራትም በሶሪያ ቀጣይ ላይ የሚመክሩ መድረኮችን ሲያደርጉ ነበር፡፡
እሑድ እለት በሳዑዲ ዐረቢያ ሪያድ ከተማ፤ የሳዑዲ ዐረቢያ፣ ግብጽ፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች፣ ኳታር፣ ባሕሬን፣ አራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ኢራቅ፣ ሊባኖስ እና ቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተሳተፉበት በሶሪያ ጉዳይ የመከረ ጉባዔ አከናውናዋል፡፡ ይህ ጉባዔ ከአውሮፓ ሀገራት የብሪታንያ እና ጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችንም ያሳተፈ ነበር፡፡ ከጉባዔው መጠናቀቀቅ በኋላ የሳዑዲ ዐረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በሶሪያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በተመሣሣይ የአውሮፓ ኅብረት አባል የሆኑ ስድስት ሀገራት በሶሪያ ላይ የተጣለው ማእቀብ እንዲነሳ በይፋ ጠይቀዋል፡፡
ስለ ሶሪያ ወቅታዊ ሁኔታ ያነሱት አዲሱ የሀገሪቱ መሪ፤ የአሰድን መኮብለል ተከትሎ ደማስቆ ዳግም ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ መቀላቀል መጀመሯን በመግለጽ፤ “የተገኘውን ዕድል ማባከን እንደማይገባ” አሳስበዋል፡፡ በተለይ ተብለው ከተቀመጡ ሁኔታዎች ውጪ ለሁሉም “ምሕረት ማድረግ” አስፈላጊ እንደሆነ በማንሳት ይህን በመተግበር በድጋሚ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ያለመግባት ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
አል ሻራ የምሕረትን አስፈላጊነት ቢያነሱም በሀገሪቱ የቀድሞ አገዛዝ ወቅት በተለይ በ“ሰደንያ” ወሕኒ ቤት ውስጥ በርካታ ወንጀል በመፈጸም የሚጠረጠሩ ባለሥልጣናት ጉዳይ በዚህ አግባብ የሚታይ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ በሕጋዊ መንገድ ፍትሕ ሊሰፍን እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም እነዚህን ጉዳዮች ባሉበት መተው “ለበቀል በር ከፋች” መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በቃል ምልልሱ ላይ የተነሳው ሌላኛው ጉዳይ በተለያዩ ሀገራት በስደት የሚገኙ ሶሪያዊያን እጣ ፋንታ ነው፡፡ በዚህም በቀጣይ ሁለት ዓመታት አብዛኞቹን የሀገራቸውን ዜጎች የመመለስ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ “ደካማ” ተብሎ የተፈረጀውን የሶሪያ ፓስፖርት ወደቀደመ አቅሙ መመለስ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡












