Homeዜናና ወቅታዊዜናየልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከልን አገልግሎት ለማሻሻል መላው ኅብረተሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠቅላይ...

የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከልን አገልግሎት ለማሻሻል መላው ኅብረተሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ጥሪ አቀረበ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምከር ቤት፤ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ በተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ይህ ጥሪ የቀረበው ዛሬ ሐሙስ ታኅሣሥ 24/2017 የምክር ቤቱን ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ የመሩት ቡድን በማዕከሉ ተገኝቶ ጉብኝት ባካሔደበት ወቅት ነው፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ለምክር ቤቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል የሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የማዕከሉ የቦርድ ሊቀመንበር በአቶ ሰላሐዲን ኸሊፋ የማዕከሉን የአገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል፡፡

ከማዕከሉ ጉብኝት በኃላ የተናገሩት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ ማዕከሉን እገዛ እንደሚፈልግ በመግለጽ በቀጣይ ምክር ቤቱን ጨምሮ ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በቅርቡ ከሙስሊም ኤድ አሜሪካ የተገኙ ወደ ስምንት መቶ ሚሊዮን ብር ገደማ ግምት ያላቸው የሕክምና ቁሳቁሶችን ለጤና ተቋማት ልገሣ እንዲደረግ በማስተባበር ተሳትፎ ማድረጉን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ተመሳሳይ ድጋፎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በዛሬው እለት በምክር ቤቱ ኃላፊዎች ጉብኝት የተደረገለት በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ፤ የተመሠረተው በ1982 ነው፡፡ ማዕከሉ በሺሕዎች ለሚቆጠሩ ሕፃናት የልብ ቀዶ ሕክምና በነፃ የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት በመጀመሪያዎቹ 20 ዓመታት ውስጥ 2 ሺሕ 600 ታካሚዎችን ወደ ውጭ አገር መላኩን ገልጿል፡፡

ከ2001 ጀምሮ በአዲስ አበባ የራሱ የልብ ሕክምና ማዕከል በመክፈት ተጨማሪ 6 ሺሕ 400 ታማሚዎችን ሲያክም ከ20 ሺሕ በላይ በክትትል እና 8 ሺሕ አሁንም በመጠባበቂያ ዝርዝር ውስጥ እንደሚገኙ አሳውቋል፡፡ ማዕከሉ የተመሠረተው በዶክተር በላይ አበጋዝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular