የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ በትግራይ ክልል አክሱም በሙስሊሞች መብት ላይ ጥሰት በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ጠየቀ። ምክር ቤቱ በአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከትምሕርት ገበታ እንዲሆኑ መደረጉ መፍትሔ ያገኛል በሚል በትዕግሥት ቢጠብቅም እልባት አለመገኘቱን ገልጿል።
ምክር ቤቱ በአክሱም በሙስሊሞች መብት ላይ ጥሰት በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ የጠየቀው ዛሬ ረቡዕ ታኅሣሥ 23/2017 በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ላይ የሚፈጸሙ የመብትና የሃይማኖት ጥሰቶችን በሚመለከት ባወጣው መግለጫ ነው።
በዚህ መግለጫ ላይ በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ሃይማኖታዊ ትንኮሳዎች የመንግሥት አካላትን ጨምሮ የሥጋት ምንጭ እየሆኑ እንደሚገኙ ተገልጿል። ከዚህ አንጻር የአክሱም ከተማ ትምህርት ቢሮ በትምህርት ቤቶች የሙስሊም ሴት ተማሪዎችን ከአለባበስ ጋር በተገናኘ ለአንድ ወር ገደማ ከትምህርት ገበታ አስተጓጉለዋል ብሏል። አንዳንድ ተማሪዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ የሚጠቅሰው መግለጫው፤ በከተማው ሙስሊሞች ለዘመናት የነበረባቸው የእምነት ነፃነት፣ የመስገጃ ቦታ ችግርና የቀብር ቦታ እጦት ወደ ባሰ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ጠቁሟል።
መግለጫው አክሎም የክልሉና የፌዴራል መንግሥት የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በዓለም አቀፍ ሕግጋትና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27 የተቀመጡ መብቶችን የሚሸረሽሩ ተግባራትን መፈፀማቸውን አውግዟል።
ምክር ቤቱ በጠቀሰው በአክሱም ከተማ ሴት ተማሪዎች በትምሕርት ቤቶች በተጣለው ሒጃብ ክልከላ ምክንያት ከትምሕርት ገበታ ውጪ የሆኑት ከታኅሣሥ 8/2017 አንስቶ ነው፡፡
በከተማው በተማሪዎች ላይ የሒጃብ ክልከላውን ጥለውታል የተባሉት ትምህርት ቤቶች በቀጥር ቢያንስ አምስት ናቸው፡፡ ትምሕርት ቤቶቹ “አክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት”፣ “አሉሚናይ”፣ “ወርኣይ”፣ “ክንደያ” እና “ኣብርሃ ወ ኣጽብሃ” መሆናቸውም ታውቋል፡፡
በትምሕርት ቤቶቹ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሀገር አቀፍ ፈተና ቅጽ የሚሞሉበት ጊዜ ታኅሣሥ 14/2017 የጀመረ ቢሆንም፤ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከትምሕርት ገበታ ውጪ ለመሆን በመገደዳቸው መሙላት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ በሒጃብ ክልከላው ምክንያት በተለይ “ወርኢይ” በተሰኘው ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ ሴት ተማሪዎች፤ የሴሚስተር አካፋይ (Mid semester) ፈተና ላይ መቀመጥ ሳይችሉ መቅረታቸው ታውቋል፡፡












