የፍልስጤሙ ሐማስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ታዛቢ ቡድን ወደ ጋዛ በመግባት ለሆስፒታሎች ከለላ እንዲሰጥ ጥሪ አቀረበ፡፡ ቡድኑ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በፍልስጤም “ታይቶ የማይታወቅ” ወንጀል ሲፈጸም በዝምታ መመልከቱን ተችቷል፡፡
ሐማስ ይህን ጥሪ ያቀረበው አዲስ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የታዛቢ ቡድን እንዲገቡ ጥሪ ያቀረበው፤ ከእስራኤል ወታደሮች ጥቃት የተረፉ የጤና መሠረተ ልማቶች ጥበቃ እንዲደረግላቸው በሚል ነው፡፡
ቡድኑ በመግለጫው፤ የእስራኤል ወታደሮች የአየር ላይ ጥቃት ሰንዝረው በአልዋፋ ሆስፒታል እና በማዕከላዊ ጋዛ ከተማ የሚገኘውን ባፕቲስት የተሰኘው ሆስፒታል ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን “የጦር ወንጀል” እና “የዓለም አቀፍ ሕጎች ጥሰት” ነው ሲል አውግዟል።
በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “ታይቶ የማይታወቅ ወንጀል እና የዘር ማጥፋት ሲፈጸም” እንዲሁም በሆስፒታሎች እንዲሁም በጤና ባለሞያዎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም፤ በዝምታ መመልከቱንም በመተቸት ድምጹን እንዲያሰማ ወትውቷል፡፡
የሐማስ መግለጫ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ተቋማቱ እነዚህን ወንጀሎች ለማስቆም አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስዱ፣ የተዛቢ ቡድን እንዲልኩ፣ ለሆስፒታሎች እና ለሕክምና ማዕከላት ጥበቃ እንዲደረግ እናንዲሁም በወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን መጠየቁን የቁድስ ፕረስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ሐማስ መግለጫ ያወጣው የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛ ሆስፒታል ነው የሚባለውን የከማል አድዋን ሆስፒታል ላይ ከበባ በመፈጸም ዳይሬክተሩን ዶክተር ሑሳም አቡ ሱፊያን ጨምሮ 240 ሰዎችን ማገታቸውን ከተገለጸ በኋላ ነው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት ዳሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ድርጊቱን አውግዘውታል፡፡
በጋዛ የሚገኙ ሆስፒታሎች በድጋሚ የጦር ሜዳ ተደርገዋል ያሉት ዶክተር ቴድሮስ፤ የጤና ሥርዓቱ አደጋ ውስጥ መውደቁንም በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል፡፡ አክለውም በሆስፒታሎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












