Homeዜናና ወቅታዊዜናበጋዛ የሚፈጸመውን የዘር ፍጅት ለማስቆም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአስቸኳይ ርምጃ እንዲወስድ ጥሪ...

በጋዛ የሚፈጸመውን የዘር ፍጅት ለማስቆም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአስቸኳይ ርምጃ እንዲወስድ ጥሪ ቀረበ

በፍልስጤም ጋዛ የሚፈጸመውን የዘር ፍጅት ለማስቆም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአስቸኳይ ርምጃ እንዲወስድ ጥሪ ያቀረበው፤ ዓለም አቀፍ የሙስሊም ምሑራን ኅብረት ነው፡፡ ኅብረቱ ርምጃው እንዲወሰድ ጥሪ ያቀረበው በዋና ጸሐፊ ዶክተር ዓሊ ሙሐመድ አልሶላቢ በኩል ነው፡፡  

ዋና ጸሐፊው ስለ ጉዳዩ በተናገሩበት መግለጫ፤ “በፍልስጤም ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ መታገስ የሚቻል አይደለም” ብለውታል፡፡ አያይዘውም “ስለ ሰላም፣ መረጋጋትና የሰብዓዊ መብቶች መከበር እንታገላለን የሚሉ አካላት በኃይል ሚዛን አሰላለፍ ከፊት ረድፍ በተቀመጡበት ዓለም” ይህን መመልከት “ሊታመን የማይችል” መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ዓሊ ሙሐመድ አልሶላቢ ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ በጋዛ በከበባ ውስጥ ቆይተው፤ ላለፉት 15 ወራት የዘር ፍጅት እያስተናገዱ የሚገኙ ፍልስጤማዊያን፤ በአሁኑ ሰዓት የተጋረጠባቸውን አደጋም ዓለም በዝምታ መመልከቱንም በመግለጫቸው ኮንነዋል፡፡

በዋና ጸሐፊው እንደ ሥጋት የተጠቀሰው ጉዳይ በጋዛ ረሐብ ደቅኗል የተባለው የምግብ እጥረት እና የመጠለያ እጦት ነው፡፡ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በዚህ ሳምንት ይዘዋቸው በወጡ ዘገባዎች፤ በፍልስጤም በአሁኑ ሰዓት ባለው የአየር ጠባይ ምክንያት ቅዝቃዜው የበረታቸው ሕፃናት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ፍልስጤማዊያን እየተጋፈጡት ለሚገኙት ችግር ተጠያቂው “እስራኤል እና ገንዘብ እንዲሁም የጦር መሣሪያ የሚያስታጥቋት ሀገራት” ብቻ ሳይሆኑ፤ “የሙስሊም እና ዐረብ ሀገራትም ጭምር” መሆናቸውንም በመጥቀስ ተችተዋል፡፡ የዐረብ እና ሙስሊም ሀገራት ላይ ትችታቸውን የሰነዘሩት፤ ፍልስጤማዊያን ችግር ውስጥ ከተዘፈቁበት ችግር ነጻ ለማውጣት ከጎን ባለመቆም ነው፡፡ አክለውም “ረብ የለሽ ነው” ያሉትን በፍልስጤም የሚሰነዘረውን ጥቃት ማስቆም ካልተቻለ፤ ዳፋው ከቀጣናው አልፎ ለቀሪው ዓለም የሚተርፍ ነው መሆኑን በመጠቆም ጥቃቱ እንዲቆም አሳስበዋል፡፡

ዶክተር ዓሊ ሙሐመድ አልሶላቢ በዋና ጸሀፊነት የሚያገለግሉበት ዓለም አቀፍ የሙስሊም ምሑራን ኅብረት የተመሠረተው፤ እ.አ.አ በ2004 ነው፡፡ ዋና መቀመጫውን በኳታር እና አየርላንድ ደብሊን ያደረገውን ኅብረት በመሥራችነት የሚጠቀሱት፤ ከሁለት ዓመት ወደ አኺራ የተሻገሩት ግብጻዊው ሸይኽ ዩሱፍ አል ቀርዷዊ ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular