Homeዜናና ወቅታዊዜናየአል ነጃሺ መስጂድ የዕድሳት ሥራ 52 በመቶ መድረሱን የቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ...

የአል ነጃሺ መስጂድ የዕድሳት ሥራ 52 በመቶ መድረሱን የቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ አስታወቀ

በትግራይ ክልል የሚገኘው የአል ነጃሺ መስጂድ የዕድሳት ሥራ 52 በመቶ መድረሱን ግንባታውን በገንዘብ የሚደግፈው የቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ቲካ) አስታውቋል፡፡ በግንባታው ሒደት ቀድሞ ጉዳት ደርሶበት የነበረው የመስጂዱ ጉልላት ዕድሳት እንደተደረገለት ታውቋል፡፡

የግንባታውን ወጪ የሚሸፍነው የቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ፤ የመስጂድ የዕድሳት ሥራ በአሁኑ ሰዓት 52 በመቶ መድረሱን ያስታወቀው በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው መረጃ ነው፡፡ ኤጀንሲው፤ ሥራው “ከግንባታ ባሻገር ታሪክን፣ ባሕልን እና ማንነትን የማስጠበቅ” ተግባር መሆኑን ገልጿል፡፡ የዕድሳት ሥራውን በተመለከተ በተሠራጨው የፎቶግራፍ መረጃ ቀድሞ ጉዳት ያስተናገዱ የመስጂዱ ሌሎች ክፍሎችም ግንባታቸው እየተከናወነ ይገኛል፡፡

የአል ነጃሺ መስጂድ ዕድሳት የተጀመረው መስከረም 13/2017 እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ “ሚንበር ቲቪ” በወቅቱ በግንባታ ላይ ከሚሳተፉ ባለሞያዎቹ እንደሰማው ከሆነ፤ የዕድሳት ሥራውን ለማጠናቀቀቅ የተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ ስምንት ወር ነው፡፡

የመስጂዱ ዕድሳት ሥራ ከፊል ገጽታ/TIKA

ሥራው እየተከናወነ የሚገኘው በትግራይ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ በሚያደርገው በቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ አማካኝነት ነው፡፡ ሥራው በዋነኝነት በሁለቱ አካላት ትብብር የሚከናወን ቢሆንም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እንዲሁም የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ተሳታፊ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

የግንባታውን ወጪ የሚሸፍነው የቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ቲካ)፤ በሀገሪቱ የባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኝ የልማት መምሪያ ነው፡፡ ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም በተመሣሣይ የመስጂዱን ዕድሳት ለማከናወን እየሠራ በነበረበት ወቅት፤ በክልሉ ጦርነት በመከሰቱ ምክንያት ሥራውን ማቆሙ ተነግሯል፡፡ በ2013 በክልሉ በነበረው ጦርነት ወቅት በመስጂዱ ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ ዕድሳቱን በድጋሚ ለማከናወን፤ ከስምንት ወራት በፊት ከትግራይ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል፡፡

የመስጂዱ ዕድሳት ሥራ ከፊል ገጽታ/TIKA

መስጂዱ በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ያስተናገደው በውስጠኛው ክፍል፣ በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች መቃብር እና በእልፍኙ ነበር፡፡ እየተከናወነ የሚገኘው የዕድሳት ሥራ እነዚህን ጨምሮ በዝናብ እና ሌሎች ሁኔታዎች የደረሰውን ጉዳት የሚያካትት ነው፡፡

የአል ነጃሺ መስጅድ፤ ከትግራይ ክልል ዋና መቀመጫ መቐለ ከተማ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ታሪካዊውን መስጂድ በዩኒስኮ ለማስመዝገብ እየተሠራ መሆኑንም ከወራት በፊት የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ የትግራይ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጥምረት ባዘጋጁት በመስጂድ መልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ ኮንፍረንስ ላይ ተነግሯል፡፡ በ4 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው አል ነጃሺ መስጅድ፤ ዋናውን መስጂድ እንዲሁም ሁለት የቀብር ሥፍራዎችን በውስጡ ይዟል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular