Homeዜናና ወቅታዊዜናበግብጽ ያልጠበቁት የገጠማቸው ሶሪያዊያን ስደተኞች

በግብጽ ያልጠበቁት የገጠማቸው ሶሪያዊያን ስደተኞች

ከአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር 90 በመቶው ሙስሊም በሆነባት ሶሪያ፣ ለሩብ ክፍለ ዘመን ገደማ ሀገሪቱን የመሩት ፕሬዝዳንት በሻር አል አሰድ ከኮበለሉ ሁለት ሳምንት ደፈነ። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሶሪያን ከመሩበት አጠቃላይ የጊዜ ርዝማኔ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ያሳለፉት ሀገራቸውን እንዳልነበር ባደረገ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ነው።

በዚህ ጊዜ ከ13 ሚሊዮን በላይ ሶሪያዊያን ሀገራቸውን ጥለው ለስደት ተዳርገዋል። በመጨረሻ ግን በዜጎች ላይ ሲደርስ የቆየው የስደት እጣ እርሳቸውም አገኛቸውና እንደ ሌሎች ሶሪያዊያን ሰው ቤት አደሩ፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት ከተጠለሉበት ሞስኮ ሆነው በጻፉት ደብዳቤ፤ “ሀገሬን ጥዬ የኮበለልኩት አስቤበት አይደለም፤ እስከመጨረሻው በደማስቆ በሥራ ላይ ነበርኩ፤ ዘግየት ብዬ ነው ከወዳጅ የሩስያ ሰዎች ጋር ወደ ወደብ ከተማዋ ላዛቂያ ያመራሁት” ብለዋል፡፡ አሳድ ወደ ሞስኮ የበረሩት በወደብ ከተማዋ በኩል አድርገው ነበር ተብሏል፡፡

የቀድሞው ፕሬዝዳንት በዚህ ደብዳቤ በአገዛዝ ዘመናቸው ስለተቀጠፉት ነፍሶች፣ ስለቆሰለ አካል ወይም ስለተሰሰዱ ዜጎች አንድም ቦታ ላይ የፀፀት አልያም የይቅርታ ቃል አላሠፈሩም፡፡ ባይሆን “ሁሉንም ነገር ያደረግኩት ለሀገሬ እና ለሕዝቧ ጥቅም ነው” ብለዋል፡፡ ተቃዋሚዎቻቸውን ለመግለጽ በተደጋጋሚ የተጠቀሙት ቃል “አሸባሪ” የሚለውን ነው፡፡ የበሻር ደብዳቤ “ሶሪያ አንድ ቀን በድጋሚ ነጻነቷን መጎናጸፏ አይቀርም የሚል ተስፋ አለኝ” የሚል መስመር የተካተተበትም ነው፡፡

በአንጻሩ በአሰድ አገዛዝ ወቅት በተለያዩ የዓለም ሀገራት የተበተኑ ዜጎች የሀገራቸው ፕሬዝዳንት መኮብለላቸው ከተሰማበት ከኅዳር 29/2017 አንስቶ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል፡፡ እ.አ.አ በ2011 ሶሪያዊያኑ በይፋ የተመዘገበ ቁጥራቸው 21 ሚሊዮን ነበር፡፡ ከእነዚያ ዜጎች መካከል 14 ሚሊዮኑ በመላው ዓለም ተበትነዋል፡፡ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ላይመለሱ በወታደሮች ተገድለዋል፡፡ ከግድያ የተረፉትን በርካታ ዜጎች ያስጠለሉት ቱርክ፣ ሊባኖስ፣ ዮርዳኖስ እና ኢራቅ ናቸው፡፡ ጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ስዊድን እና ግሪክ ከአውሮፓ ይጠቀሳሉ፡፡ ሶሪያዊያኑ ወደ አፍሪካም አምርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ እና ካይሮ ጉዳናዎች ዜጎቹን ማየትም አዲስ አልነበረም፡፡ በተለይ የአውሮፓ ሀገራት ሶሪያዊያኑን ከዚህ በኋላ በጥገኝኘት አንቀበልም ከማለት ውጪ አሁንም ድረስ ስለመመለስ አልያም አለመመለሳቸው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አልደረሱም፡፡

ሶሪያዊያኑ ከተጠለሉባቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል የሰሜን አፍሪካዋ ግብጽ ያሳለፈችው ውሳኔ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ በግብጽ የሚገኙ የሶሪያ ዜጎች በሻር አል አሰድ ደማስቆን ለቀው መኮበለላቸው ሲሰማ በሌሎች የዓለም ሀገራት እንደሚገኙት ሁሉ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ይህ የደስታ አገላለጽ በግብጽ መንግሥት አልተወደደም፡፡ ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ከወጡት መካከል ቢያንስ 30 ሶሪያዊያንን ፖሊስ ወደ እስር ቤት አስገብቷቸዋል፡፡ ፖሊሲ በሶሪያዊያኑ ላይ በትር መሰንዘሩንም ኢጂፕሽያን ኢኒሼቲቭ ፎር ፐርሰናል ራትስ የተሰኘ የሀገሪቱ የመብቶች ተሟጋች ድርጅት አሳውቋል፡፡ በትር ካረፈባቸው በተጨማሪ አሁንም ድረስ በእስር ላይ የሚገኙት ሶሪያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲባረሩ ውሳኔ ሊተላለፍባቸው መሆኑንም ገልጿል፡፡ የግብጽ መንግሥት ለምን እዚህ ውሳኔ ላይ እንደደረሰ እስካሁን ድረስ የሰጠው ማብራሪያ የለም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular