“ሚንበር ቲቪ” እና “ሚላን ሚዲያ” በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት የተፈራረሙት በዛሬው እለት ነው፡፡ የፊርማ ሥነ ሥርዐቱ ዛሬ ሰኞ ታኅሣሥ 14/2017 በሚንበር ቲቪ ዋና መሥሪያ ቤት ተከናውኗል፡፡ በሚንበር ቲቪ በኩል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አዩብ አደም እንዲሁም ሚላን ሚዲያን በመወከል ደግሞ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓብዱልመሊክ ሰይፈዲን ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡
በስምምነቱ ላይ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አዩብ አደም፤ ጣቢያው ከዚህ ቀደም ከሚላን ሚዲያ ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎች በጋራ ሲሠራ መቆየቱን በማስታወስ፤ የዛሬው ስምምነት በተለይ ሚንበር ቲቪ በተለያዩ የቋንቋ አማራጮች ወደ ተመልካቾች ለመድረስ የሚያደርገውን ጥረት በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስምምነቱ የተደረገው በሚላን ሚዲያ አማካኝነት በጣቢያው በኦሮሚኛ ቋንቋ የሚዘጋጁ መሰናዶዎች ለማቅረብ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሉባት ሀገር መሆኗን በመጥቀስም፤ በቀጣይ በሌሎች ቋንቋዎች የተለያዩ ይዘቶችን ከሚያዘጋጁ አካላት ጋር ተመሳሳይ ስምምነቶችን ለማድረግ በሚንበር ቲቪ በኩል እቅድ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ጣቢያው ለሌሎች የፕሮዳክሽን ድርጅቶችም ክፍት በመሆኑ ፍላጎቱ ያላቸው እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዛሬው እለት ከሚንበር ቲቪ የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመው ሚላን ሚዲያ፤ በኦሮሚኛ ቋንቋ በሚያዘጋጃቸው ይዘቶች ባለፉት ዓመታት ዋና መሥሪያ ቤቱን በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ በማድረግ ሲሠራ የቆየ ነው፡፡ የፕሮዳክሽን ድርጅቱ ባለፈው ወር በሸገር ከተማ ያስገነባውን አዲስ ስቱድዮም አስመርቋል፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርዐቱ ላይ የተናገሩት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓብዱልመሊክ ሰይፈዲን፤ ሚላን ሚዲያ መዝናኛን ጨምሮ ሌሎች ያልተዳሰሱ ጉዳዮችን በሚንበር ቲቪ ለማቅረብ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ሚንበር ቲቪ በተመሳሳይ ከአንድ ወር በፊት በተማሪዎች እና ወጣቶች ዙርያ ከሚሠራው “ከሙስሊም ተማሪዎች ሊግ” ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል፡፡












