የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በከተማው ውስጥ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የኢማም ዓሊ መስጂድና የአዳሪ ትምሕርት ቤት ግንባታ ማስጀመሩን አስታወቀ።
ዛሬ ቅዳሜ ታኅሣሥ 12/2017 የማስጀመሪያ መርሐ ግብር የተከናወነለት የዓሊዩ መስጂድና የአዳሪ ትምሕርት ቤት፤ ከሐበሺስታን ማኅበርና ከቬረነል የትብብር ማኅበር ጋር በመቀናጀት የሚሠራ መሆኑን ምክር ቤቱ ባወጣው መረጃ ገልጿል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ የምክር ቤቱ ኃላፊዎች፣ በዛሬው እለት የተጀመረውን ዓሊዩ መስጂድና አዳሪ ትምሕርት ቤት ተጠናቆ የታሰበው ግብ እስኪሳካ የማይቋረጥ እገዛና ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸዋል ተብሏል። የአካባቢው ማኅበረሰብም የሚጠበቅበትን እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የቬረነል ማኅበር ተወካዮችም መስጂዱን ለመሥራት የተነሱት “ኢትዮጵያ ለሙስሊሙ ዓለም እና ለእስልምና መስፋፋት ባደረገችው ውለታ ነው” ማለታቸው ተጠቅሷል። ግንባታው “የንጉሥ ነጃሺና የቢላል ኢብን ረባህን ውለታ ለመመለስ የሚደረግ ነው” ተብሏል። (ሚንበር ቲቪ)












