በዓለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ፊፋ እ.አ.አ በ2034 የሚዘጋጀውን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ የተመረጠችው ሳዑዲ ዐረቢያ፤ በውድድሩ ወቅት በስታዲየሞች የአልኮል መጠጥ እንደማታቀርብ ባለሥልጣናት መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
ይህንኑ የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ከፊፋ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሰምቻለሁ ብሎ ዘግቧል፡፡ ፊፋ ሳዑዲ ዐረቢያ የዓለም ዋንጫ እንድታዘጋጅ መመረጧን ይፋ ያደረገው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ የእግር ኳስ አስተዳዳሪው ይህን ካሳወቀ በኋላ በተለይ የምዕራብ ዓለም መገናኛ ብዙኃን፤ ሀገሪቱ በእስላማዊ ሕጎች እንደምትተዳደር በመጥቀስ በውድድሩ ሒደት የአልኮል መጠጥ ክልከላ ሊጣል ይችላል በሚል ቀድመው ተቃውሞ አዘል ዘገባዎችን ሲያሠራጩ ቆይተዋል፡፡
የእንግሊዙ ጋዜጣ ሥማቸውን ያልጠቀሳቸው የፊፋ ከፍተኛ ባለሥልጣን፤ ሳዑዲ ዐረቢያ ከአስር ዓመት በኋላ ለሚካሔደው ውድድሩ ከአሁኑ አልኮል በስታዲየሞች ውስጥ መሸጥ እንደማይቻል ውሳኔ አሳልፋለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከሀገሪቱ ጋር መልካም ግንኙነት አላቸው የሚባሉት የፊፋ ባለሥልጣናት ምንም እንኳን ከአልኮል መጠጥ አምራቾች ጋር የንግድ ሽርክና ቢኖራቸውም የሀገሪቱን አቋም ለማስቀየር ሙከራ የማድረግ እቅድ አለመያዛቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡ የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት የተመረጠችው ሳዑዲ ዐረቢያ፤ የአልኮል መጠጥ በሀገሪቱ እንዳይሸጥ ክልከላ የጣለችው እ.አ.አ በ1952 ነው፡፡
የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ከፊፋ ጋር ባላቸው ቅርበት ምክንያት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ይነገራል፡፡ የሳዑዲ ዐረቢያው ብሔራዊ የነዳጅ አምራች “አርማኮ” ከፊፋ ጋር ለአራት ዓመት የሚቆይ የ320 ሚሊዮን ፓዉንድ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ የሳዑዲ ዐረቢያ ፐብሊክ ኢንቨስትመንት ፈንድ የፊፋን የክለቦች ውድድር የቀጥታ ሥርጭት ለመውሰድ “ዳዝን” በተሰኘው ኩባንያ በኩል 800 ሚሊዮን ፓዉንድ ክፍያ ፈጽሟል፡፡
የዓለም ዋንጫ ከሁለት ዓመት በፊት በተመሣሣይ በሌላኛዋ እስላማዊ ሀገር ኳታር መስተናገዱ የሚታወስ ነው፡፡ ኳታር በውድድሩ ወቅት በስታዲየሞች የአልኮል መጠጥ እንደማፈቀድ ያስታወቀችው የመክፈቻው ጨዋታ ከመደረጉ ሁለት ቀን አስቀድሞ ነበር፡፡ እስልምና የመንግሥት ሃይማኖት በሆነባት ኳታር፤ በውድድሩ ላይ ስለ እስልምና የሚሰነዘሩ አሉታዊ አስተያቶች ከፍተኛ ቅጣት እንደሚያስከትሉ ድንጋጌ አስቀምጣ ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












