Homeዜናና ወቅታዊዜናመገናኛ ብዙኃን ለበጎ አድራጎት ማኅበራት የሚያደርጉትን እገዛ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

መገናኛ ብዙኃን ለበጎ አድራጎት ማኅበራት የሚያደርጉትን እገዛ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

መገናኛ ብዙኃን ልዩ ፍላጎት ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያደርጉትን እገዛ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የተጠየቀው ዛሬ ማክሰኞ ታኅሣሥ 8/2017 የሚንበር ቲቪ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በዓብደላ ኢብን ኡሚ መክቱም የቁርኣን ማኅበር እና በየሲር ለና በጎ አድራጎት ድርጅት ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡ የሥራ ኃላፊዎቹ ጉብኝት ካደረጉባቸው ማኅበራት መካከል የዓብደላ ኢብን ኡሚ መክቱም የቁርኣን ማኅበር ለዐይነ ስውራን ዜጎች የተለያዩ ድጋፎችን የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚሁ ወቅት የተናገሩት የሚንበር ቲቪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዩብ አደም፤ የሥራ ኃላፊዎቹ ጉብኝት ካደረጉባቸው ድርጅቶች መካከል በተለይ በዓብደላ ኢብን ኡሚ መክቱም የቁርኣን ማኅበር በአብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል የዘነጋቸውን ወገኖች እያገለገለ እንደሚገኝ በማስታወስ፤ ይህን ይበልጥ የማገዝ የሁሉም ድርሻ መሆኑን በመጥቀስ መገናኛ ብዙኃንም ከዚህ ቀደም ሲያደርጉ የቆዩትን እገዛ አጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል፡፡

በዛሬው ጉብኝት ወቅት ሚንበር ቲቪ ከዚህ ቀደም ያደርጋቸው ከነበሩ የማስታወቂያ እና ሌሎች ድጋፎች በተጨማሪ በስሩ በሚገኘው የ“ሚንበር ሪከርድስ” የተዘጋጀውን የአራቱን ኸሊፋዎች ታሪክ የያዘ በጥራት የተቀናበረ የመጽሐፍ የድምጽ ቅጂ በሥጦታ በኃላፊዎቹ በኩል ለማኅበሩ አስረክቧል፡፡

በሚንበር ቲቪ የሥራ ኃላፊዎች የተደረገውን ጉብኝት በተመለከተ የተናገሩት የዓብደላ ኢብን ኡሚ መክቱም የቁርኣን ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ኸድር ማሕሙድ፤ ማኅበራቸው ከሚሠራባቸው ጉዳዮች መካከል የድምጽ የተዘጋጁ መጻሕፍትን ማቅረብ መሆኑን በመግለጽ፤ በሚንበር ቲቪ በዛሬው እለት በነጻ የተበረከተላቸው የአራቱ ኸሊፋዎች ታሪክ መጽሐፍ በማኅበሩ ስር ለታቀፉ ዐይነ ስውራን ዜጎች ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዛሬው የጉብኝት መርሐ ግብር ላይ የጣቢያው የሥራ ኃላፈዎች በተመሣሣይ በእውቁ የእስልምና መምሕር ኑሩ ቱርኪ የሚመራውን “የሲር ለና የበጎ አድራጎት ማኅበር” መጎብኘት ችለዋል፡፡ ወላጅ አጥ ሕጻናትን፣ አረጋዊያንን እና ሴቶችን የሚደግፈው ድርጅት፤ በልብስ ባንክ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የጉድጓድ ውሃ በማስቆፈር የሚታወቅ ነው፡፡ ስለ ሥራ ኃላፊዎቹ ጉብኝት የተናገሩት የድርጅቱ የየሲር ለና በጎ አድራጎት ድርጅት መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ ኑሩ፤ የሥራ ኃላፊዎቹ ጉብኝት በተለይ የመገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ ጉልሕ ከመሆኑ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚኖረው መሆኑን አስረድተው ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

በየሲር ለና ከተደረገው ጉብኝት በኋላ የተናገሩት የሚንበር ቲቪ የአርት እና ፕሮዳክሽን ማናጀር አቶ ሙሐመድ ፈረጅ፤ ጣቢያው በቴሌቪዥን ለበጎ አድራጎት ማኅበራት በየዓመቱ ሰፊ የአየር ሰዐት በነጻ በመስጠት እንዲሁም ምርኩዝን በመሳሰሉ የመድረክ አማራጮች የማስተዋወቅ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸው በቀጣይም ከሌሎች የበጎ አድራጎት ማኅበራት ጋር ይህንኑ አጠናክሮ የመቀጠል አላማ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular