Homeዜናና ወቅታዊዜናከወለድ ነጻ ባንኮችን በተመለከተ በመመሪያ ገደብ የተጣላቸው አሠራሮች በአዲሱ የባንክ ረቂቅ አዋጅ...

ከወለድ ነጻ ባንኮችን በተመለከተ በመመሪያ ገደብ የተጣላቸው አሠራሮች በአዲሱ የባንክ ረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ አልተደረገባቸውም በሚል በፓርላማ ጥያቄ አስነሳ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነጻ ባንኮችን በተመለከተ በመመሪያ ገደብ የተጣላቸው አሠራሮች በአዲሱ የባንክ ረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ አልተደረገባቸውም በሚል በፓርላማ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ፤ አዋጁ “የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ሴኩላር መሆኑን ታሳቢ ባደረገ መልኩ” አጠቃላይ የሸሪዓ አስተዳደርን ለመቆጣጠር የሚያስችል መመሪያ ማዘጋጀት የሚያስችል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ ከወለድ ነጻ ባንኮችን በተመለከተ በመመሪያ ገደብ የተጣላቸው አሠራሮች በአዲሱ የባንክ ረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ አልተደረገባቸውም በሚል በፓርላማ ጥያቄ የቀረበው ዛሬ ማክሰኞ ታኅሣሥ 8/2017 በተካሔደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው፡፡ በተደረገው ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን በ11ኛ መደበኛ ስብሰባ ጥያቄ የተነሳበት የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጁ ለምክር ቤቱ ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦበት ጸድቋል፡፡

በስብሰባ ላይ ጥያቄ ያቀረቡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል፤ በሀገሪቱ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሠጡ ባንኮች ‘በመመሪያ ገደብ ምክንያት ሁሉንም የባንክ አሠራር እና ሕጎች ተከትለን እየሠራን አይደለም’ የሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ አዲሱ የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅም ከዚህ ቀደም የነበሩ ቅሬታዎችን የሚፈታ አይደለም ያሉት የፓርላማ አባሉ፤ ይህ የመመሪያ ገደብ “ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ባንኮችም ችግር የሚፈጥር” መሆኑን ጠቁመው በጉዳዩ ላይ ከብሔራዊ ባንክ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ጥያቄውን ያቀረቡት የፓርላማ አባል

በሌላ በኩል የፓርላማ አባሉ ከዚሁ ጥያቄ ጋር አያይዘው ያነሱት ጥያቄ፤ ብሔራዊ የሸሪዓ ባንክን የሚመለከት ክፍል እንደሌለው በማንሳት ከዚህ አንጻር ባንኩ በቀጣይ ምን ዐይነት እቅድ አለው የሚል ነው፡፡

ከፓርላማ አባሉ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምሕረቱ፤ የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ሁለት ዐይነት አካሔድ አንደሚኖረው በመጠቆም፤ አንደኛው መደበኛ ቀሪው ደግሞ ሸሪዓን መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ገዢው ጨምረውም የአዲሱ የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 81ን በመጥቀስ፤ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች “ፍቃድ የሚሰጥበትን፣ ቁጥጥር የሚደረግበትንና ሌሎች ሁኔታ እና መስፈርቶችን የሚወስንበትን” መመሪያ እንደሚያወጣ በግልጽ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡ “የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ሴኩላር መሆኑን ታሳቢ ባደረገ መልኩ” አጠቃላይ የሸሪዓ አስተዳደርን ለመቆጣጠር የሚያስችል መመሪያ ሊወጣ እንደሚችል መቀመጡንም አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ

ይህ አዋጅ ከፓርላማ አባላት ጠይቄ ቀርቦበት ምላሽ እና ማብራሪያ ከተሰጠበት በኋላ በሦስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ከቀረቡት ሁለት ረቂቅ አዋጆች መካከል በተመሣይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በሀገሪቱ በአሁኑ ሰዓት ከሚሰበሰበው አጠቃላይ ሐብት ውስጥ 10 በመቶው ከወለድ ነጻ አሠራር የሚገኝ ነው፡፡ በባንኩ የባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ቁጥር ስምንት ደርሷል። በመስኮት ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡት ደግሞ ሠላሳ ገደማ ናቸው። በባንኮቹ የተከፈተው ሒሳብ 22.5 ሚሊዮን ሲሆን፣ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 232.71 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በብድር የተሰጠው 104 ቢሊዮን ደርሷል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular