Homeዜናና ወቅታዊዜናከወሌ ሙሐመድ መስጂድ ጋር የተያያዘው ከመቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው ቅርስ የመፍረስ...

ከወሌ ሙሐመድ መስጂድ ጋር የተያያዘው ከመቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው ቅርስ የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠበት ምክር ቤቱ ገለጸ

የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ በከተማው በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የሚገኘው የወሌ ሙሐመድ መስጂድ አጠገብ የሚገኘው የ119 ዓመት ዕድሜ ያለው በቅርስነት የተመዘገበ መኖሪያ ቤት የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠበት ገለጸ። በቅርስነት የተመዘገበው መኖሪያ ቤት ንብረትነቱ መስጂዱን ያስገነቡት የሐጂ ወሌ ሙሐመድ መሆኑ ታውቋል።

ምክር ቤቱ ታሪካዊው የሐጅ ሙሐመድ ወሌ መኖሪያ ቤት ላይ የመፍረስ አደጋ ተጋርጧል ያለው ዛሬ ሰኞ ታኅሣሥ 7/2017 ነው። እንደ ምክር ቤቱ ከሆነ መኖሪያ ቤቱ የመፍረስ አደጋ የተጋረጠበት “መንግሥት በወረዳው እያከናወነው ካለው የልማት ስራ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ያሉ ግንባታዎችን ሁሉ እያፈረሰ” በመሆኑ ነው።

በታሪካዊው በወሌ ሙሐመድ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች ቤቱን እንዲለቁ መደረጉን የሚገልጸው የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መግለጫ፣ መኖሪያ ቤቱ በአሁኑ ሰዓት በቅርበት ጥበቃና ክትትል እየተደረገለት አለመሆኑንም ይገልጻል። ይህ ደግሞ “በቤቱ የተለያዩ ክፍሎች ላይ ዝርፊያ እንዲፈጸምበት እያደረገው” እንደሚገኝ ጠቁሟል።

በአካባቢው ያለው የልማት እንቅስቃሴ “ቤቱን ታሳቢ የማያደርግና ጥንቃቄ የማይወሰድ” ከሆነም የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ቅርስ የሆነው ይህ ታሪካዊ ቤት “በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈርስ እንደሚችል” ገልጿል።

የወሌ ሙሐመድ ቅርስ ተጠብቆ እንዲቆይ ያሳሰበው ምክር ቤቱ፣ መኖሪያ ቤቱ የተጋረጠበትን አደጋ በመጥቀስ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኅዳር 30/2017 ደብዳቤ መጻፉን ቢያሳውቅም የተገኘ ምላሽ ስለመኖሩ የገለጸው ነገር የለም።

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular