በሙስሊም ተማሪዎች ሊግ የተዘጋጀው “ፋቲሕ ኮንቬንሽን” የመጀመሪያ ዓመት መርሐ ግብር የተከናወነው በአዲስ አበባ ከተማ ነው። “የሃይማኖት እሴቶች እና የትምሕርት ተቋማት በኢትዮጵያ” በሚል ርእስ በተከናወነው መርሐ ግብር ላይ ተጋባዥ እንግዶች ንግግር ሲያቀርቡ፣ የፓናል ውይይቶችም ተካሔደዋል።
ትናንት ቅዳሜ ታኅሣሥ 5/2017 የተከናወነው መርሐ ግብር የቀረበው በአዲስ አበባ ከተማ ዋልያ ቡክስ ነው። በዚህ ኮንቬንሽን ላይ ስድስት ግለሰቦች ንግግር አቅርበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በአራት ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት ተካሔዷል። እነዚህ የፓናል ውይይቶች በትምሕርት ተቋማት ውስጥ የሚከወኑ ተግባራት ያላቸው ዓለም አቀፍ ተመክሮ፣ ሃይማኖታዊነትና ሥነ ምግባር ለመደበኛ ትምህርት ስኬት ያለው አስተዋፅኦ፣ የእምነትና የአለባበስ ነፃነት በትምሕርት ተቋማት ከሕግ እና ሰብዓዊ መብቶች አንጻር እንዲሁም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የትምሕርት ተሳትፎ ከታሪክ እና ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የሚዳስሱ ነበሩ።
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ፕሬዝዳንት ኡስታዝ ሐይደር ኸድር እንዲሁም ሙስሊም ምሑራን ከሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ተማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ተማሪዎች ጀመዐ አሚሮች ተገኝተዋል።
የፋቲሕ ኮንቬንሽን አዘጋጅ የሙስሊም ተማሪዎች ሊግ፤ በተለይ ተማሪዎች እና ወጣቶችን በተመለከቱ ዝግጅቶች የሚታወቅ ነው። በየዓመቱ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ሽልማት እንዲሁም የተለያዩ ሥልጠናዎችን ለወጣቶች የሚሰጥም ነው። ፋቲሕ ኮንቬንሽንን በየዓመቱ ለማከናወን በእቅድ መያዙን አዘጋጆቹ ገልፀዋል። (ሚንበር ቲቪ)












