Homeየቲቪ ፕሮግራሞችበኡስታዝ አቡበከር አሕመድ አስተባባሪነት ከሙስሊም ኤይድ አሜሪካ የተገኘ 800 ሚሊዮን ብር የሚገመት...

በኡስታዝ አቡበከር አሕመድ አስተባባሪነት ከሙስሊም ኤይድ አሜሪካ የተገኘ 800 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሕክምና ቁሳቁስ ለሆስፒታሎች በድጋፍ ተሰጠ

በዕውቁ የእስልምና መምሕር አቡበከር አሕመድ አስተባባሪነት ከሙስሊም ኤይድ አሜሪካ የተገኘ 800 ሚሊዮን ብር የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስ ለሆስፒታሎች በድጋፍ የተሰጠው በዛሬው እለት ነው፡፡

ዛሬ ጁመዓ ታኅሣሥ 4/2017 በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ቅጽር ግቢ በተከናወነው መርሐ ግብር ላይ አስተባባሪው ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ተወካይ እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የሕክምና ቁሳቁሶቹን ድጋፍ በተመለከተ የተናገሩት ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፤ ሙስሊም ኤይድ ድጋፉ ሲያደርግ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ድረስ በአጠቃይ 15 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ መደረጉን ያስታወሱት ኡስታዝ አቡበከር፤ በዚህም የሕክምና ግብዐቶች እና መድኃኒቶች ለሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ለማዳረስ ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በዚህኛው ዙር ድጋፍ የ‘ኢመርጀንሲ ኪት’ ድጋፍ የተደረገላቸው ለአምስት የክልል ሆስፒታሎች መሆኑ ተገልጿል፡፡ እነዚህም ድል ጮራ ሆስፒታል ድሬዳዋ፣ የአሶሳ ሆስፒታል፣ የጅግጅጋ ሆስፒታል፣ የሥልጤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና የሙሁር አክሊል የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ናቸው፡፡ ለእያንዳንዳቸው እንዲደርስ የተደረገው የሕክምና ቁስ ድጋፍ 1 ሚሊዮን 240 ሺሕ ዶላር የሚገመት መሆኑም በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡

ሙስሊም ኤድ አሜሪካ በቀጣይ የሚያደርገው ድጋፍ ይቀጥላል የተባለ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት 5 ኮንቴይነር የሕክምና ግብዐት ጅቡድቲ መድረሱንም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ ይህ ግብዐት በቀጣይ ትግራይን ጨምሮ ለሌሎችም ክልሎች የሚዳረስ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ከጤና ሚኒስቴር የሚኒስትሯ ተወካይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል፡፡ በዚሁ ንግግራቸው በኡስታዝ አቡበከር አሕመድ አስታባሪነት የሙስሊም ኤድ ድጋፍ ከዚህ ቀደም በተመሣሣይ መደረጉን አስታውሰው፤ ለድጋፉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ድጋፉ በዚህ የመጨረሻ እንደማይሆንም ተስፋ እንደርጋለን ሲል ገልጸዋል፡፡

በሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መርሐ ግብሩ ላይ በአስተባባሪው የሕክምና ቁሳቁሶች በፍጥነት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ “ከፍተኛ ኃላፊነት ተወጥቷል” በሚል የተገለጸው የኢትዮጵያ እሰልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ንግግረ አድርገዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር የተደረገው ድፍ በአግባቡ ለሚመለከተው የኅብረተሰብ ክፍል መድረሱን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ የአደራ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡  

እ.አ.አ በ1985 የተመሠረተው ሙስሊም ኤይድ አሜሪካ፤ በተለያዩ አካቢዎች የተፈጥሮ አደጋዎች ወይም ግጭቶች ሰለባ የሆኑ ወይም በድህነት፣ በረሐብ፣ በበሽታ፣ በፍትህ መጓደል፣ በኢኮኖሚ ዕድሎች እጦት ለሚሰቃዩ ሰዎች እርዳታ የሚሰጥ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅት መሆኑንመ የሚገልጽ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular