Homeዜናና ወቅታዊዜናየጀርመን ባለሥልጣናት ሙስሊሞችን በሚመለከት አሉታዊ አመለካከቶችን ከማሠራጨት እንዲቆጠቡ የመብት ተሟጋቹ አስጠነቀቀ

የጀርመን ባለሥልጣናት ሙስሊሞችን በሚመለከት አሉታዊ አመለካከቶችን ከማሠራጨት እንዲቆጠቡ የመብት ተሟጋቹ አስጠነቀቀ

ዕውቁ የጀርመን የሰብዓዊ መብቶች ተቋም (ዲአይኤምአር) የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ሙስሊሞችን በሚመለከት አሉታዊ አመለካከቶችን ከማሠራጨት እንዲቆጠቡ አስጠነቀቀ። በጀርመን 1 ሺሕ 926 ፀረ ሙስሊም የጥላቻ ክስተቶች መመዝባቸው ተገልጿል።

የመብት ተሟጋቹ ድርጅት ማስጠንቀቂያውን ያወጣው አዲስ ባወጣው ሪፖርት ነው፡፡ ድርጅቱ በሀገሪቱ ውስጥ ፀረ ሙስሊም አመለካከት እና የጥላቻ ወንጀሎች እየጨመሩ መምጣታቸውንም ገልጿል፡፡

ቡድኑ በዋነኝነት በጋዛ ቀጠና ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የእስራኤል ባለሥልጣናት በጋዛ የሚፈጽሙትን የዘር ማጥፋት በተመለከተ ይፋ ባደረገው ባለ 32 ገጽ ሪፖርት፤ ፀረ እስልምና ክስተቶች ቁጥር መጨመሩን በመግለጽ ሥጋቱን አጋርቷል።

ይኸው ሪፖርት በመላው ዓለም ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብ መሪዎች እና የመገናኛ ብዙኃን ስለ ሙስሊሞች አሉታዊ አመለካከቶችን ከማስፋፋት እንደቆጠቡም ጥሪ አቅርቧል፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ቡድን ዳይሬክተር ባተ ሩዶልፍ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ ሙስሊሞችን በተመለከተ የሚሰጡ ጥቅል አስተያየቶች በፍልስጤማዊያን እንዲሁም በአጠቃላይ በሙስሊሞች ላይ ጥላቻ እያስፋፋ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በጀርመን ከባለፈው ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ አንስቶ ፍልስጤምን የሚደግፉ የአደባባይ ሠልፎች ላይ ፖሊስ ክልከላ ጥሏል፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ የፍልስጤማዊያን ግንድ ያላቸው ዜጎች አደባባይ ላይ ወጥተው ተቃውሟቸውን የመግለጽ መብታቸው በመገደቡ ከጋዛ ንጹሐን ጎን መቆማቸውን የሚያሳዩበትን ዕድል ሊያገኙ አልቻሉም፡፡

የዲአይኤምአር ሪፖርት እንደሚያሳየው ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በጀርመን 1 ሺሕ 926 ፀረ ሙስሊም የጥላቻ ክስተቶች የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም በአማካይ በቀን አምስት አጋጣሚዎች እንደሚመዘገቡ የሚጠቁም ነው፡፡ የፀረ ሙስሊም የጥላቻ ክስተቶች ከሁለት ዓመት በፊት በ2022 ከተመዘገበው 114 በመቶ መጨመሩን ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡

በቪየና የሚገኘው የአውሮፓ ኅብረት የመሠረታዊ መብቶች ኤጀንሲ (ኤፍአርኤ) በአውሮፓ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሙስሊሞች ባለፉት አምስት ዓመታት አድልዎ እንደተፈፀመባቸውና በመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት እየጨመረ በመምጣቱ ሁኔታው በፍጥነት እየተባባሰ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ኤፍአርኤ በሪፖርቱ “በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ሙስሊም መሆን አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል” ሲል የሁኔታውን አስከፊነት ገልጿል።

የ2023 ጥናት እንደሚያሳየው ከጀርመን አጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ የሙስሊሞች ቁጥር 6.6 በመቶ ይይዛል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular