ጀርመን እና ስዊድንን ጨምሮ አምስት የአውሮፓ ሀገራት ከሶሪያ ዜጎች የሚቀርብ የጥገኝነት ጥያቄ ላይ እግድ መጣላቸውን አስታወቁ፡፡ ቱርክ በበኩሏ ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ የሶሪያ ዜጎች “የአንድ ጊዜ ነጻ የጉዞ ትኬት” አዘጋጅቻለሁ ብላለች፡፡
የአውሮፓ ሀገራት የሶሪያ ዜጎች የሚያቀርቡትን የጥገኝነት ጥየቄ ማገዳቸውን ያስታወቁት፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሻር አል አሰድ አገዛዝ መውደቁን ተከትሎ ነው፡፡ የፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚ ኃይሎች እሑድ ንጋት ላይ መዲናዋ ደማስቆን መቆጣጠራቸውን ይፋ ከማድረጋቸው አስቀድሞ በሻር አል አሰድ ሀገራቸውን ጥለው ወደ ሞስኮ መኮብለላቸውን የሩስያ መገናኛ ብዙኃን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
የአል አሰድ አገዛዝ መውደቅ ይፋ ከተደረገ በኋላ፤ ከአውሮፓ ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ የሶሪያ ዜጎችን ተቀብላለች የምትባለው ጀርመን፤ ከዚህ በኋላ የሶሪያዊያንን የጥገኝነት ጥያቄ እንደማትቀበል በባለሥልጣናቷ በኩል ገልጻለች፡፡
እየጠናቀቀ በሚገኘው እ..አ.አ በ2024 ጀርመን የ72 ሺሕ ጥገኝነት ጠያቂ ሶሪያዊያንን ጥያቄ መቀበሏን ይፋ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል 47 ሺሕ የሚደርሱት ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሚገኙ የአልጀዚራ ዘገባ ያመለክታል፡፡ አዲሱ አሠራር ምላሽ እየተጠባበቁ በሚገኙት ላይ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችልም ዘገባው ጠቅሷል፡፡ ጀርመን በተለይ ለ13 ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ በቆየችው ሶሪያ ቀውሱ በተባባሰበት ወቅት በርካታ ስደተኞችን መቀበሏ ይነገራል፡፡
የጀርመን ጎረቤት ኦስትሪያም እንዲሁ ተመሣሣይ ውሳኔ ማሳለፏን ያስታወቀችው አል አሰድ መውደቃቸው ከተሰማ 48 ሰዓታት ሳይሞላ ነው፡፡ የሀገሪቱ ቻንስለር ካርል ኒሃመር፤ ሰኞ በሰጡት መግለጫ የጥገኝነት ጥያቄ ያቀረቡ ሶሪያዊያን ጥያቄ ታግዷል ብለዋል፡፡ በኦስትሪያ በአሁኑ ሰዓት ወደ 100 ሺህ ገደማ ሶሪያዊያን እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡

ስዊድን፣ ኖርዌይ እና ዴንማርክም የሶሪያዊያንን የጥገኝነት ጥያቄ መቀበል እንዳቆሙ የገለጹት “ሐያት ተሕሪዝ አል ሻም” የተሠኘው ቡድን ደማስቆን መቆጣጠሩን ከገለጸ በኋላ ባለው አጭር በሚባል የጊዜ ርዝማኔ ነው፡፡ ፈረንሳይ ደግሞ በቀጣይ እንደ ጀርመን እና ቀሪዎቹ ሀገራት ተመሣሣይ ውሳኔ እንደምታሳልፍ የሀገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡
በሌላ በኩል ባለፉት ዐስር ዓመታት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የሶሪያ ዜጎች ጥገኝነት ሰጥታለች የምትበለው ቱርክ፤ ወደ ሀገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ሶሪያዊያን “የአንድ ጊዜ ብቻ” ትኬት በነጻ አዘጋጅቻለሁ ማለቷን የሀገሪቱ መገናና ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ቱርክ ይህን ያቀረበችው በከተማ ከንቲባዎች አማካኝነት ነው፡፡
ለአንድ ጊዜ ጉዞ ብቻ የሚያገለግል የነጻ ትኬት አዘጋጅቻለሁ ባለችው ቱርክ፤ ዜጎች በቅርብ ዓመታት ለተፈጠረው የኑሮ ውድነት እና ተዛማጅ ችግሮች ሶሪያዊያን ከፍተኛ አድርገዋል በሚል ቅሬታ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ በዚህም በ2021 የሶሪያዊያንን የንገድ ተቋማት እና መኖሪያ ቤቶች ኢላማ ያደረገ ተቃውሞ ተነስቶ ወደ አመጽ ተቀይሮ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡
ሀገራቱ ውሳኔያቸውን ከማሳለፋቸው ጎን ለጎን መግለጫ ያወጡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ፤ ከስደተኞቹ ጋር በተገናኘ ውሳኔ ለማሳለፍ በሶሪያ ያለውን ውስጣዊ ሁኔታ በንቃት እና በትዕግሥት መከታተል እንደሚገባ በመናገር ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
በሶሪያ በ2011 በጀመረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ከ14 ሚሊዮን በላይ የሀገሪቱ ዜጎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የዓለም ሀገራት ለመበተን መገደዳቸው ይታወቃል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2024 ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ የሶሪያ ዜጎችን በዋነኝነት ያስጠለሉት ጎረቤቶቿ ሊባኖስ፣ ዮርዳኖስ፣ ኢራቅ እና ቱርክ ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












