Homeዜናና ወቅታዊዜናበተማሪዎች የምግብ በጀት ተመን ላይ ከነገ ጀምሮ ማሻሻያ ሊደረግ ነው

በተማሪዎች የምግብ በጀት ተመን ላይ ከነገ ጀምሮ ማሻሻያ ሊደረግ ነው

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፤ የተማሪዎች የምግብ በጀት ተመን ላይ ከነገ ጀምሮ 100 ብር እንደሚደረግ ገለጸ፡፡ ማሻሻያውን የጠየቀው ትምሕርት ሚኒስቴር፤ በቀጣይ የሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የምግብ ሜኑ ተመሣሣይ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተማሪዎች የምግብ በጀት ተመን ላይ ከነገ ጀምሮ 100 ብር እንደሚደረግ የገለጸው ለትምሕርት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ኅዳር 25/2017 በጻፈው ደብዳቤ ላይ የትምሕርት ሚኒስቴር በመስከረም ወር መገባደጃ የተማሪዎች የምግብ በጀት “ከወቅቱ ገበያ አኳያ ተማሪዎችን ለመመገብ በቂ ባለመሆኑ” ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተመን ማሻሻያ ጥናት መደረጉን አስታውሷል፡፡ የቀረበውን የምግብ በጀት ተመን ማሻሻያ ጥናት ከወቅቱ ገበያና ከመንግሥት የመክፈል አቅም አኳያ በማየትም የምግብ በጀት ተመን በቀን በአንድ ተማሪ የነፍስ ወከፍ ወጪ 100 ብር እንዲሆን ውሳኔ መተላለፉን ገልጿል፡፡

በደብዳቤ ላይ “የሁሉም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የምግብ አቅርቦት በወጥነት እንዲከናወን” ያሳሰበው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፤ ከምግብ በጀት ተመን ማሻሻያው ጋር የተጣጣመ ስታንዳርድ “የምግብ ሜኑ” እንዲዘጋጅም ጥብቅ መመሪያ አስተላልፏል፡፡

ይህንኑ ተከትሎ የትምሕርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት የምግብ ሜኑ ተመሳሳይ እንዲሆን ውሳኔ መተላለፉን ዛሬ ሰኞ ኅዳር 30/2017 ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡ በጉዳዩ ላይ የተናገሩት በትምሕርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሠረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ፤ ወቅታዊ የምግብ ዋጋ ንረትን ግምት ውስጥ በማስገባት የምግብ በጀት ማስተካከያ መደረጉን ገልጸዋል። በሀገሪቱ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ያለው የምግብ ሜኑ ተቀራራቢ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ሰለሞን በአዲሱ የበጀት ተመን መሠረት ለዩኒቨርስቲዎቹ ባላቸው ተማሪ ቁጥር ልክ ገንዘቡ እንደሚለቀቅላቸው ጠቁመዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በመንግሥት ተገንብተው ተማሪዎችን በራሳቸው ወጪ እያስተናገዱ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በተያዘው ዓመት የሚመደበው የምግብ በጀት ካልተስተካከለ ምግብ ማቅረብ አዳጋች እንደሚሆንባቸው አስታውቀው ነበር፡፡ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ጥያቄ ሲያቀርቡበት የቆየው ለአንድ ተማሪ የሚመደበው የአንድ ቀን ወጪ 22 ብር ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular