Homeዜናና ወቅታዊዜናየሙስሊም መራጮችን ልብ “ያሸፈቱት” ትራምፕ

የሙስሊም መራጮችን ልብ “ያሸፈቱት” ትራምፕ

ያለፉትን ቀናት የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ዋንኛ ትኩረት ሆኖ የቆየው የአሜሪካ ምርጫ ዛሬ ረቡዕ አሸናፊው ታውቋል፡፡ አወዛጋቢው የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ዶናልድ ትራምፕ ማሸነፋቸው ምርጫውን በሚያስተዳድረው አካል በይፋ ተገልጿል፡፡ በርግጥ ቀድሞ ውጤቱን ይፋ ያደረገው ወግ አጥባቂው የመገናኛ ብዙኃን ፎክስ ኒውስ ነበር፡፡ የሰውዬው ማሸነፍ ዘግየት ብሎም ቢሆን እንደ ቢቢሲ ባሉ መገናኛ ብዙኃንም ተስተጋብቷል፡፡

በይፋዊ የድምጽ ቆጠራ ውጤቶች እስካሁን ድረስ ዶናልድ ትራምፕ ከ71 ሚሊዮን በላይ መራጮችን ድምጽ በማግኘት 51 በመቶ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ በአንጻሩ ካማላ ሐሪስ ያገኙት ድምጽ 66 ሚሊዮን ያክል ነው፡፡

ባለፉት ወራት ሁለት ጊዜ ከጥይት የተረፉት ትራምፕ፣ ማሸነፋቸውን ሲያውጁ “ከፍተኛ ችግር ውስጥ”  ተዘፍቃለች ያሏትን ሀገራቸውን “ለማከም” እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ በምርጫው የተሸነፉት የዴሞክራቲክ ፓርቲዋ ካማላ ሐሪስ ውጤቱ ከሚጠብቁት ተቃራኒ በመሆኑ ቀድሞ የተያዘውን ለደጋፊዎቻቸው ሊያደርጉት የነበረውን ንግግር “በይደር ይቆይልኝ” ማለታቸውን ቃል አቀባያቸው ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል፡፡

በዛሬው እለት ቁርጡ በታወቀው በአሜሪካ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከፍተኛ የውይይት አጀንዳ ሆነው ከሰነበቱ ጉዳዮች መካከል ሙስሊም መራጮች ለማን ድምጻቸውን ይሰጣሉ የሚለው ነበር፡፡ መራጮቹን ለውሳኔ እንዲቸገሩ አድርጎ የነበረው የፍልስጤማዊያን አጀንዳ ነው፡፡ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች የተሸኘውን የዴሞክራቶችን አስተዳደር ‘ለእስራኤል ከፍተኛ መሣሪያ በማቅረብ ቢመረጥም የተለየ አቋም እንደማያራምድ አስመስክሯል’ ሲሉ ቆይተዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕም የተለየ አቋ ስለማያንጸባርቁ ሦስተኛ አማራጭ ካለ መታየት ይኖርበታል በሚል በእስልምና መምሕራን ጭምር ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም በሦስተኛ አማራጭነት ሥሙ ተደጋግሞ የተነሳው ጂል ስቴይን የሚመሩት ግሪን ፓርቲ ነበር፡፡ ለጂል ስቴይን ቅስቀሳ የተደረገው በምርጫው ተጽዕኖ እንደማይኖረው ቢታወቅም ኩርፊያን ለመግለጽ ነበር ይላሉ ተንታኖች፡፡

የምርጫው ውጤት ይፋ ሲደረግ በተለይ ዐረብ አሜሪካዊያን አሉት ሚባለው ሚቺጋን ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሙስሊም መራጮች ቅስቀሳ እንደተደረገው ባይሆንም ከ2020 አንጻር ለስቴይን የሰጡት ድምጽ በርከት ብሎ ተመዝግቧል፡፡ በሚቺጋን ቀደም ብሎ በወጣ የምርጫ ውጤት መግለጫ ከፍተኛ ድምጽ ያስመዘገቡት ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው፡፡

በግዛቷ ዴርቦርን አካባቢ ትራምፕን የመጡ ሰዎች አሐዝ 47 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ካማላ ሐሪስ 27 በመቶ ሲያገኙ፣ ጂል ስቴይን 21 መቶ ድምጽ ማግኘት ችለዋል፡፡ በሚቺጋን ትራምፕ ከምርጫው አስር ቀናት አስቀድሞ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ኢማሞችን መድረክ ላይ በመጋበዝ ውዳሴ ሰጥተው ሲቀበሉ ታይተዋል፡፡ በታዋቂው ኢማም ቢላል አልዙሐይሪ “አምላክ ለምክንያት ነው ያቆያቸው” የሚል ምሥክርነት የተሰጣቸው ትራምፕ፣ በቀጣይ በጋዛ ጉዳይ ምን አዲስ ነገር ይዘው ይመጣሉ የሚለው ጉዳይ ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በርግጥ ሰውዬው በዛሬው እለት ንግግራቸው ጦርነቶችን እናስቆማለን ቢሉም የጋዛን ሥም ግን አልጠሩም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular