Homeዜናና ወቅታዊዜናከሙስሊም ሴት ተማሪዎች አለባበስ ጋር በተገናኘ “ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ምክር ሐሳብ” ለማቅረብ...

ከሙስሊም ሴት ተማሪዎች አለባበስ ጋር በተገናኘ “ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ምክር ሐሳብ” ለማቅረብ መስማማቱን ምክር ቤት ገለጸ

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ ከሙስሊም ሴት ተማሪዎች አለባበስ ጋር በተገናኘ “ምክረ ሐሳብ” ለማቅረብ ከስምምነት ላይ መደረሱን በዛሬው እለት አስታወቀ፡፡ ምክር ቤቱ የሚያቀርበው ምክረ ሐሳብ ከፌዴራል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጋር በአንድነት የሚዘጋጅ መሆኑንም ገልጿል፡፡

የከተማዋ እስልምና ጉዳዮ ከፍተኛ ምክር ቤት ይህን የገለጸው ከሰሞኑ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከተፈጸመው የኒቃብ ክልከላ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ኃላፊዎች በኩል ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ ከሠላም እና ፀጥታ ዘርፍ እንዲሁም ከፖሊስ ጋር ውይይት ማድረጉን ካሳወቀ በኋላ ነው፡፡ የምክር ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሪያድ ጀማል በከተማው ውስጥ ከሚገኙት ከእነዚህ የመንግሥት አካላት ተወካዮች ጋር በተደረገው ውይይት፤ የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምክረ ሐሳብ እንዲዘጋጅ ከስምምነት ላይ መደረሱን ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 21/2017 ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡ “በምን መልኩ ይፈታ የሚለውን ምክረ ሐሳብ ነው የምናቀርብላቸው” ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ምክር ቤቱ የሚሰጠው “ፈትዋ” እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጥቅምት 16/2017 ለከተማዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ፤ ሙስሊም ሴት ተማሪዎችን ኒቃብ በመልበሳቸው ምክንያት ከትምሕርት ገበታ ውጭ መደረጋቸውን አስታውቆ ነበር። ቀድሞ በወጡ መረጃዎች ክልከላውን የጣሉት በከተማዋ ውስጥ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ትምሕርት ቤቶች ቁጥር ሰባት ነው የተባለ ቢሆንም አቶ ሪያድ ጀማል ግን ብዛታቸው “አምስት ብቻ” ነው ብለዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በመርካቶ አካባቢ የሚገኘው አዲስ ከተማ እንዲሁም የካቲት 23 እና ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል፡፡

በትምህርት ቤቶቹ ኒቃብ በመልበስ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከቆዩት ውስጥ በይፋ ቁጥራቸው ያለተጠቀሰ ተማሪዎች፤ “የተማሪዎች መተዳደሪያ ደንብ ከሚፈቅደው ውጪ በሆነ መንገድ” ኒቃብ አድርገው በመገኘታቸው ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውና በዚህም ከትምህርት ገበታ ውጪ ለመሆን መገደዳቸውን ትምህርት ቤቶቹ የሚገኙበት ክፍለ ከተማ የእስልምና ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ አመልክቷል፡፡ ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታ ውጪ ከተደረጉ ሁለት ሳምንት ማለፉንም ተያይዞ ተገልጿል፡፡

የከተማዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ግን አሁን ከትምህርት ገበታ ውጪ የተደረጉ ተማሪዎችን በተመለከተ “[ከትምህርት] ከመገለላቸው በፊት ይስተናገዱ በነበረበት ሁኔታ” ተመልሰው እንዲከታተሉ ከስምምነት ተደርሷል ብሏል። በጉዳዩ ላይ ለ“ሚንበር ቲቪ” የተናገሩት አቶ ሪያድ ከክልከላው በፊት እንደ ትምህርት ቤቶቹ ዐይነት “የአጭር ጊዜ መፍትሔ ተደርጎ ተይዞ ነበር” ባሉት “በጭንብል (ማስክ)” እንዲሁም ኒቃብ በመልበስ ተማሪዎች ወደ ክፍል ይገቡ እንደነበር በማስታወስ፤ በቀጣይ ከትምህርት ቤቶቹ እና ተማሪዎች ጋር በተደረሰ ስምምነት መሠረት እንዲቀጥሉ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ትናንት ረቡዕ ጥቅምት 20/2017 ከአዲስ ከተማ ት/ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች ጋር ውይይት ማድረጉንም አስታውቋል፡፡

ባለፉት ሳምንታት በከተማዋ በሚገኙ ትምሕርት ቤቶች ኒቃብ ለሚለብሱ ተማሪዎች በተሰጣቸው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ላይ ጥሰውታል የተባለው የተሻሻለው “የተማሪዎች መተዳደሪያ ደንብ” አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 5 ነው፡፡ ሆኖም እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ለትምሕርት ቢሮ በጻፉት ደብዳቤ፣ በትምሕርት ቢሮ የተጠቀሰው የዲሲፕሊን መመርያ ላይ “አንድም ቦታ ላይ ክልከላ የሌለበት” መሆኑን አረጋግጠዋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular