በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምሕርት ቤቶች ውስጥ በአለባበስ ምክንያት ከትምሕርት ገበታ የተፈናቀሉ ተማሪዎች መብት ተጠብቆ እንዲመለሡ የከተማው እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጠየቀ። “በአንዳንድ ኃላፊነት በጎደላቸው አመራሮች ምክንያት ችግር በሚፈጥር መልኩ” እየተኬደ ነው ያለውን ድርጊት ኮንኗል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ይህን ያለው ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 19/2017 ለከተማው አስተዳደር ትምሕርት ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ ነው። የፕሬዝዳንቱ ሸይኽ ሡልጣን አማን ፊርማ ያረፈበት ደብዳቤ፣ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ በከተማዋ አንዳንድ ትምሕርት ቤቶች ውስጥ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች “በአለባበሳቸውና በእምነታቸው ላይ ያነጣጠረ” ጫና እና እንግልት እየደረሰ መሆኑን የሚገልጽ ነው።
ችግሩ ከተከሰተበት እለት አንስቶ በወረዳ እና ክፍለ ከተማ መዋቅር ለመፍታት “ጥልቅ ውይይት” መደረጉንም ይገልጻል። ደብዳቤው ከተወሰኑ ትምሕርት ቤቶች ጋር “በተደረገ ስምምነት” ተማሪዎች ወደ ትምሕርት እንዲመለሱ ተደርጎ ከቀናት በኋላ ትምሕርት ቤቶቹ ከስምምነቱ በመውጣት በድጋሚ ክልከላ እንደተጣለባቸው የሚያትት ነው።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጥቅምት 16/2017 ለከተማዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ ሙስሊም ሴት ተማሪዎችን ኒቃብ በመልበሳቸው ምክንያት ከትምሕርት ገበታ ውጭ መደረጋቸውን አስታውቆ ነበር። ቀድሞ በወጡ መረጃዎች ክልከላውን የጣሉት በከተማዋ ውስጥ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ትምሕርት ቤቶች ብዛት ሰባት ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል በመርካቶ አካባቢ የሚገኘው አዲስ ከተማ እንዲሁም የካቲት 23 እና ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል፡፡
“ሚንበር ቲቪ” የተመለከተው በየካቲት 23 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምሕር የተፈረመት ደብዳቤ፤ መግፊራ ዓሊ የተባለች የ11ኛ ክፍል ተማሪ በትምሕርት ቤቱ ቅጽር ግቢ ውስጥ “የተማሪዎች መተዳደሪያ ደንብ ከሚፈቅደው ውጪ በሆነ መንገድ” ኒቃብ አድርጋ ስለተገኘች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣት ይገልጻል፡፡ ትምሕርት ቤቱ በማስጠንቀቂያ ደብዳቤው በተማሪዋ ተጥሷል ያለው የተሻሻለው መተዳደሪያ መመርያ አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 5 ነው፡፡
ሆኖም የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ለትምሕርት ቢሮ በጻፉት ደብዳቤ፣ በትምሕርት ቢሮ የተጠቀሰው የዲሲፕሊን መመርያ ላይ “አንድም ቦታ ላይ ክልከላ የሌለበት” መሆኑን አረጋግጠዋል። የሕግ ድጋፍ የለውም ያሉትንም ድርጊት “ሕዝበ ሙስሊሙንና መንግሥትን ለማጋጨት የሚደረግ ጥረት” መሆኑን በመገንዘብ መፍትሕ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በከተማዋ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤቶች ውስጥ በኒቃብ ምክንያት ሴት ተማሪዎች ትምሕርት ካቋረጡ ሁለት ሳምንት እንደተቆጠረ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል። (ሚንበር ቲቪ)












