በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ስር በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤቶች፤ “ኒቃብ ካላወለቃችሁ መማር አትችሉም” የተባሉ ሴት ተማሪዎች ከትምሕርት ገበታ ውጪ መደረጋቸውን የገለጸው የክፍለ ከተማው እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ጉዳዩን እየተከታተለ መሆኑን የገለጸው የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ ክልከላው የተደረገባቸው ትምሕርት ቤቶቹ ቁጥር ሰባት መድረሱን አስታውቋል፡፡
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ይህን የገለጸው ጥቅምት 16/2017 ለአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በደብዳቤው ባለፉት ዓመታት በሰላማዊ መንገድ ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች “ጥቂት በሆኑ መምሕራን ቀስቃሽነት” ከትምሕርት ገበታ መፈናቀላቸውን ገልጿል፡፡
የክፍለ ከተማው እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በዚህ ደብዳቤው ሙስሊም ሴት ተማሪዎችን ኒቃብ በመልበሳቸው ምክንያት ከትምሕርት ገበታ ውጭ ያደረጉ ትምሕርት ቤቶችን ዝርዝር ይፋ ባያደርግም፤ “ሚንበር ቲቪ” ከአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊዎች እንደሰማው ቁጥራቸው ሰባት ደርሷል፡፡ ከእነዚህ መካከል በመርካቶ አካባቢ የሚገኘው አዲስ ከተማ እንዲሁም የካቲት 23 እና ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል፡፡

ትምሕርት ቤቶቹ የሚገኙበት የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ትምሕርታቸው ለማቋረጥ ተገደዋል ያላቸው ሴት ተማሪዎች፤ ቤታቸው ለመቀመጥ ከተገደዱ 15 ቀናት እንደተቆጠረ በደብዳቤው ላይ አስፍሯል፡፡ ጉዳዩን ለመፍታትም ከትምሕርት ቤቶቹ ርእሳነ መምሕራን ጋር ውይይት ማድረጉን የገለጸው ምክር ቤት፤ ከአንደኛው ትምሕርት ቤት ጋር ከስምምነት መደረሱን በመጠቆም በተለይ የደጃዝማች ዑመር ሰመተር ትምህርት ቤት አመራር “በእምቢተኝነት ፀንቶ” ሳይሳካ መቅረቱን አመልክቷል፡፡ እንደ ምክር ቤቱ ደብዳቤ ከሆነ በትምሕርት ቤቱ ርእሰ መምሕር ተማሪዎች የቀረበው ምርጫ “ማውለቅ [ወይም] መባረር” የሚል ነው፡፡ ሁኔታው ተማሪዎች ላይ የሥነ ልቡና ጫና መፍጠሩን የጠቆመው ደብዳቤው፤ ትምሕርት እያለፋቸው መሆኑንም እንዲታወቅ አሳስቧል፡፡
“ሚንበር ቲቪ” የተመለከተው በየካቲት 23 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምሕር የተፈረመት ደብዳቤ፤ መግፊራ ዓሊ የተባለች የ11ኛ ክፍል ተማሪ በትምሕርት ቤቱ ቅጽር ግቢ ውስጥ “የተማሪዎች መተዳደሪያ ደንብ ከሚፈቅደው ውጪ በሆነ መንገድ” ኒቃብ አድርጋ ስለተገኘች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣት ይገልጻል፡፡ ትምሕርት ቤቱ በማስጠንቀቂያ ደብዳቤው በተማሪዋ ተጥሷል ያለው የተሻሻለው መተዳደሪያ መመርያ አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 5 ነው፡፡ ነገር ግን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ከክፈለ ከተማ አስተዳደር፣ ከትምሕርት ቢሮ እና የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ጋር በተደረገው ውይይት መመርያው በግልጽ ኒቃብ ማድረግን እንደማይከለክል መግለጹን በማስታወስ፣ “የግል ፍላጎትን በተከተለ በሚመስል መልኩ ካላወለቁ መግባት አይችሉም” የሚል ምላሽ መሰጠቱን ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፈዎች በበኩላቸው ጉዳዩን እየተከታተሉ መሆኑን በመግለጽ፤ እስካሁን ድረስ ከተማሪዎች፣ ወላጆች፣ ከትምህርት ቤቶቹ አመራሮች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን ለ“ሚንበር ቲቪ” ገልጿል፡፡












