ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ “የዘር ማጥፋት ድርጊቶች እየፈጸመች ነው” ስትል በዓለም አቀፍ ፍ/ቤት ላቀረበችው ክስ 750 ገጽ ያለው ማስረጃ አቀረበች፡፡ ሀገሪቱ ያቀረበችው ማስረጃ እ.ኤ.አ በ1948 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸደቀውን ዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ሕጋዊ ስምምነት ጥሳለች የሚል መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሰኞ ጥቅምት 18/2017 የቀረበው የደቡብ አፍሪካ ማስረጃ፤ ለዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት እንደላከ ያስታወቀው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ ለፍርድ ቤት የተላከው ባለ 750 ገጽ ሰነድ ባለፈው ዓመት አጋማሽ በደቡብ አፍሪካ ለቀረበው የክስ ዶሴ በማስረጃነት የሚታይ ነው፡፡ በሰነዱ ላይ ተጨማሪ 4 ሺሕ ገጽ አባሪ እንደተያያዘም ተገልጿል፡፡ ነገር ግን የቀረበው የሰነድ ማስረጃም ሆነ አባሪው የዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ደንብ ስለማይፈቅድ ለሕዝብ ይፋ አይደረግም ተብሏል፡፡
ጉዳዩን የሚከታተሉ የደቡብ አፍሪካ ተወካዮች ደቡብ አፍሪካ በወቅቱ በእስራኤል ላይ ባቀረበበችው ክስ “የተፈጸሙ ወንጀሎችንና ሆን ተብለው እንዳልታየ የታለፉ ድርጊቶችን” የዘር ማጥፋት ጠባይ ያላቸው መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡ አሁን የቀረበውን ማስረጃ በተመለከተ የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫም፤ በተጠናቀረው ማስረጃ እስራኤል “የፈጸመቻቸው የዘር ማጥፋት ድርጊቶች”፣ “ድርጊቶቹን ለማስቆም አለመቻሏ” እንዲሁም “ድርጊቱን በፈጸሙት ላይ ተጠያቂነት ማስፈን እንዳልቻለች”ም የሚያሳይ ሰነድ መካተቱንም አስፍሯል፡፡
ደቡብ አፍሪካ ለቀረበው ክስ ማስረጃ ማቅረቧን ተከትሎ ባለፈው ዓመት ክሱ ሲቀርብ “መሠረተ ቢስ” ነው ያሉት የእስራኤል ባለሥልጣናት፤ እስከ ሐምሌ 21/2017 ድረስ ምላሽ እንዲያቀርቡ የጊዜ ገደብ ተቀምጦላቸዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ለቀረበው ክስ ቦሊቪያ፣ ማልዴቪስ፣ ቺሊ፣ ቱርክዬ፣ ስፔን፣ ሜክሲኮ፣ ሊቢያ፣ ኮሎምቢያ እና ኒኳራጓ ደግፈውታል፡፡ .
የተባበሩት መንግሥታት የሕግ አስፈጻሚ አካል የሆነው ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት መቀመጫውን ያደረገው ኔዘርላንድስ ሔግ ከተማ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ሀገራት መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ሲቀርብለት ምርመራ አድርጎ ብይን ይሰጣል፡፡ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ሕግ ነክ ጉዳዮች ላይ ምክር ይለግሣል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












