የእስላማዊ ትብብር ድርጅት የፓርላማ ኅብረት፤ በፍልስጤም ጉዳይ ሙስሊሙ ዓለም ባንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አቀረበ፡፡ ኅብረቱ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከተማ ፍልስጤምን የተመለከተ ስብሰባ አካሔዷል፡፡
የፓርላማ ኅብረቱ እሑድ እለት ያካሔደውን ስብሰባ ተከትሎ በወጡ መረጃዎች፤ የቱርክ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኑማን ኩርቱልሙስ፣ በስብሰባው ላይ ሙስሊም እንደ አንድ ማኅበረሰብ ከፍልስጤማዊያን ጎን መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ የሰው ልጆች ጉዳይ ነው ያሉትን የፍልስጤምን ጉዳይ ባንድነት ካልሆነ ማሳካት እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ በፍልስጤማዊያኑ ላይ የሚፈጸመውን ኢ-ፍትሐዊነት መዋጋት አይቻልም ብለዋል፡፡
አፈ ጉባኤው አክለውም ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የእስራኤል ባለሥልጣናት በፍልስጤማዊያን ላይ ያደረሱትን በደል በዘመናዊው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እጅግ አሰቃቂው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ነው ብለውታል፡፡ እስራኤል ከፍልስጤማዊያን በተጨማሪ በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ያነሱት ኑማን ኩርቱልሙስ፣ ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂው “በጽንፈኛ ሃይማኖተኛነት በተሞላ የተዛባ ስሜት” ይነዳል ያሉት የእስራኤሉ ቤንያሚን ኔታንያሁ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
ኑማን ኩርቱልሙስ በሁለቱ ሀገራት የእስራኤል ባለሥልጣናት ለሚፈጽሙት ጥቃት፤ ተዳክሟል ያሉት የሙስሊሙ ዓለም አንድነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡ ከፍልስጤም ጎን ለመቆም የሙስሊሙ ዓለም ፖለቲካዊ ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው ባንድነት መቆም አለበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እስራኤል ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በጋዛ በሰነዘረችው ጥቃት ቢያንስ 42 ሺ ንጹሐን መገደላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የጋዛ ጤና ቢሮ እንዳለው ከሆነ ከተገደሉት መካከል የእናቶች እና ሕጻናት ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












