Homeዜናና ወቅታዊዜናበውጭ ምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ መካከል ባለው ልዩነት ላይ ገደብ ተቀመጠ

በውጭ ምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ መካከል ባለው ልዩነት ላይ ገደብ ተቀመጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት በላይ ከሁለት በመቶ መብለጥ የለበትም ሲል በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡ በዚሁ መሠረት የመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዶላር መሸጫ ዋጋ ላይ በዛሬ እለት 8.24 ብር ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 5/2017 ባወጣው መግለጫ፤ በሀገሪቱ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሬ ሥርዐት ተግባራዊ ከተደረገበት ሐምሌ 2016 አንስቶ ሒደቱን ሲከታተል መቆየቱን በማሳወቅ፤ የአሠራር ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ውሳኔ ያሳለፈባቸውን ጉዳዮች ዘርዝሯል፡፡

በዚህም የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ከሁለት በመቶ መብለጥ የለበትም ያለው ብሔራዊ ባንክ፤ ይህ “በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ አሠራር” መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ከአዲሱ አሠራር ጋር በተገናኘ አሁንም ቢሆንም ባንኮች የምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ ዋጋ በልዩ ሁኔታ ከደንበኞቻቸው ጋር  ስምምነት ማድረግ ይችላሉ ብሏል፡፡ ሆኖም አካሔዱ ግልጽ እንዲሆን መመሪያ አስተላልፏል፡፡

በተጨማሪም ንግድ ባንኮች የምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ ዋጋቸውን በተናጠል በየቀኑ ማሳወቅ እንዲቀጥሉ በማስታወስ፤ ከውጭ ምንዛሬ ሽያጭ ጋር በተያያዘ የሚጠይቋቸውን ኮሚሽኖች ከምንዛሬ መሸጫ ጋር ሳይሆን በተናጠል ለደንበኞቻቸው እንዲያሳውቁ ትእዛዝ አስተላልፋል፡፡ የተሻሻለው አሠራር ለንግድ ባንኮች እንደተላከ ያስታወቀው ብሔራዊ ባንክ፤ እስከ ነገ ጥቅምት 6/2017 እንዲተገበር ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የተሻሻለው አሠራር ተከትሎ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ በዛሬው እለት በመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዶላር ከብር አንጻር ያለው ምንዛሬ በመሸጫው ዋጋ ላይ ቅናሽ ተመዝግቧል። ባንኩ የባለፈውን ሳምንት ቀናት እንዲሁም ትናንት ጥቅምት 4/2017 ድረስ አንድ የአሜሪካን ዶላር በ112.39 ሲገዛ የነበረ ሲሆን፣ መሸጫው 123.63 ነበር።

ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 5/2017 ባወጣው አዲስ ዋጋ የመግዣ ዋጋው ላይ መጠነኛ ጭማሪ በማድረግ አንድ ዶላር 113.13 እንደሚገዛ አሳውቋል። በአንጻሩ ባንኩ በመሸጫ ዋጋ ላይ ቅናሽ በማድረግ ለአንድ ዶላር 115.39 ዋጋ አስቀምጧል። በመሸጫ ዋጋ ላይ የተመዘገበው ቅናሽ 8.24 ብር ነው። የመንግስታዊው ባንክ የዛሬ መሸጫ እና መግዣ ልዩነት 2.26 ብር ሆኗል፡፡

ከግል ባንኮች ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጠው ዘምዘም ባንክ፤ በዛሬው እለት አንዱን ዶላር በ112.52 እንደሚገዛ ያሳወቀ ሲሆን፣ መሸጫው 127.14 ብር መሆኑን ገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular